በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሩዝ ምርምርና ስልጠና ማዕከል ተመረቀ

86
ባህርዳር ህዳር 6/2011 በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፎገራ የሩዝ ምርምርና የስልጠና ማዕከል በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ዛሬ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት በተኙበት ተመረቀ። በ33 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የምርምር ማዕከል በጃፓንና በኢትዮጵያ መንግስት ወጪው የተሸፈነ ነው። ማዕከሉ በውስጡ የማሰልጠኛ፣ የላቦራቶሪ፣ የምርምር ጣቢያዎች፣የተመራማሪዎች መኖሪያ ቤትና መሰል የመገልገያ ቢሮችን የያዘ ነው። የማዕከሉ ዓላማ በክልል ብሎም በሃገሪቱ ያለውን የሩዝ ሃብትን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና ዘመናዊ አሰራሮችን በመተግባር ከሃገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ነው። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት ክልሉ ሩዝን ለማምረት የሚያስችል ስነ-ምህዳር ባለቤት ቢሆንም በተሻሻለ አሰራር ባለመታገዙ አርሶ አደሩ ከምግብ ፍጆታ ማለፍ አልቻለም። ለዚህም የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የሩዝ ምርጥ ዘሮችን አለመጠቀም፣ከልማዳዊ አሰራር አለመላቀቅ፣ ተገቢውን የሙያ ድጋፍ አለማድረግና ምርታማነትን ሊያሳድግ የሚችል አሰራር አለመከተል ዋነኛ ክፍተቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል። በሃገሪቱ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በሩዝ መልማት የሚችል መሬት ሲኖር ከዚህ ውስጥ 75 በመቶውን የአማራ ክልል ይሸፍናል ያሉት ደግሞ የፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ካባ ኦርጌሳ ናቸው። "ይህን ያህል ለሩዝ ስነ-ምህዳር ተስማሚ መሬት ተይዞ ሀገሪቱ በዓመት ከ200 ሺህ ቶን በላይ ሩዝ ወደ ሃገር ውስጥ ታስገባለች" ብለዋል። ለዚህም በአማካኝ በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ይደረጋል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው የማዕከሉ መገንባት ይህንና መሰል የዘርፉን ችግሮች ይፈታል ተብሎ የታመነበት መሆኑንም ጠቁመዋል። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሰደር እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የዘርፉ ምሁራንና አመራሮች ተገኝተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም