የተጠርጣሪዎቹ መያዝ የህግ የበላይነትን ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ማሳያ ነው

105
ደሴ ህዳር 5/2011 በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሌብነት  የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዛቸው  የህግ የበላይነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተደረገ ያለው ጥረት ማሳያ መሆኑን አስተያየታቸውነ ለኢዜአ የሰጡ የደሴ ከተማ  ነዋሪዎች ገለጹ ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የወሎ ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ሰብስብ ሃዲስ እንዳሉት  በጠቅላይ አቃቤ ህግ የተሰጠው መግለጫ ላለፉት ዓመታት ህግ ከተሰደደችበት ተመልሳ ወደ መንበሯ መቀመጧን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ላለፉት ዓመታት ግለሰቦች ፍትህን በራሳቸው የመስጠት አማራጭን ይጠቀሙ  እንደነበር ገልጸው ይህም ህዝቡ በመንግሥት የዴሞክራሲና የፍትህ ተቋማት ላይ ያለው አመኔታ ዝቅተኛ እንደሆን ማድረጉን አመልክተዋል፡፡ በንድፈ ሀሳብ  ደረጃ ለተማሪዎች የሚሰጧቸው የስነ ምግባርና የስነዜጋ ትምህርት ተግባር ላይ ስለማይውል የውጭ ሀገራትን በምሳሌነት ለመጥቀስ ይገደዱ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የተጀመረውን የህግ የበላይነት ለማስቀጠል ሁሉም በተሰማራበት መስክ የድርሻውን ማበርከት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የህግ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዘላለም እሸቱ  በበኩላቸው ችግሩ ላለፉት 27 ዓመታት ሲንከባለል የመጣና ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች የተሳተፉበት ውስብስብ ወንጀል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግሥት ህልውናውን ባገኘ  በአጭር ወራት ውስጥ በወንጀል የተጠረጠሩት ግለሰቦች መያዛቸው  እንደሚደነቅ ገልጸዋል፡፡ ተጠያቂነቱ እንደ ደረጃው ይለያያል እንጂ በወንጀሉ ላይ የበርካቶች እጅ እንዳለበት የተናገሩት ምሁሩ መንግሥት የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራው ለማስቀጠል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅሮች ለሚፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂ የሚያደርግ ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ  እንዲቀጥል የሰብአዊ መብት ጥሰትን የሚከላከል ጠንካራ ፓርላማ፣ የመገናኛ ብዙኃንና  ሲቪል ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚመክሩ አክቲቪስቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግሥት ማኅበራዊ ድር ገጾች በተጠያቂነት የሚመሩበትን ስርዓት መዘርጋት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ በጥብቅና ሙያ የሚተዳደሩት አቶ ቢኒያም በቀለ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሰብአዊ መብት ጥሰትና ሌብነት ወንጀል የጠረጠራቸውን ሰዎች መያዙ  ህዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት የሚያጎለብት  መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እርምጃው ማንም ከህግ በላይ እንዳልሆነ የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመው የፍትህ ስርዓቱ የበለጠ በአስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲቆም በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደረገው የምርመራና የፍርድ ሂደት ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻና ሙያዊ ስነ ምግባርን የተከተለ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ " የጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጫ በተወሰኑ አካላት የተደረገው ከፍተኛ ምዝበራ የብዙሃኑን ጥቅም የጎዳ መሆኑን ያሳያል " ያሉት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን የመንግሥት ሰራተኛ የሆኑት አቶ እሸቱ አሊ ናቸው፡፡ አስተያየት ሰጪው እንዳሉት ላለፉት ዓመታት ህዝቡ ስለመልካም አስተዳደርና ስለ የህግ የበላይነት የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና የሚሰጣቸው መረጃዎች ተቀባይነት አልነበራቸውም፡፡ ይህም አሁን ለተከሰተው ችግር ምክንያት መሆኑን ተናግረው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  የሚመራው አዲሱ መንግሥት የህዝብን ቅሬታዎች በመስማት አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት ባህል መጎልበት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ የህዝብና የመንግስት ሃብት የመዘበሩና የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ 63 ተጠርጣሪ ወንጀለኞች መያዛቸውን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም