እርምጃው ለሀገራዊ ለውጡ ቀጣይነት ወሳኝ ነው --- በአሶሳ ከተማ አስተያየት ሰጪዎች

58
አሶሳ ህዳር 5/2011 የሰብአዊ መብት ጥሰትና ሌብነት ፈጽመዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የተወሰደው  እርምጃ ለሀገራዊ ለውጡ ቀጣይነት ወሳኝ መሆኑን በአሶሳ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነምግባር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ሙሉነህ ካሳ እንዳሉት የተፈፀሙት ወንጀሎች በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጫ በተጠቀሰው ልክ ይሆናል ብለው አልጠበቁም ፡፡ " የተደራጁ ግለሰቦች በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው የፈፀሙት በሰብአዊነት የተቃጣ ወንጀል ነው" ብለዋል፡፡ እርምጃው ወደ ታዳጊ ክልሎችም መግባት እንዳለበት የጠቆሙት  አቶ ሙሉነህ በኢንቨስትመንት ስም ከፍተኛ ምዝበራዎች በነዚህ ክልሎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡ ለውጡን አስተማማኝ ለማድረግ  የፍትህ ተቋማትን ማጠናከር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስተያታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የአሶሳ ከተማ አስተዳደር የወረዳ ሁለት ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት  ወጣት ሙስጠፋ አልማሙን በበኩሉ "የተወሰደው እርምጃ ለለውጡ ቀጣይነት አስፈላጊ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብሏል፡፡ ወጣቱ እንዳመለከተው የተፈፀሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመንግስት አካል ደረጃ ይፈፀማሉ ተብሎ የማይጠበቁ ዘግናኝ ድርጊቶች ናቸው፡፡ በዜጎች ላይ አሰቃቂ ወንጀልና  የህዝብን ሃብት መዝብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የመያዙ ስራ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡ የሀገር ሃብት በተደራጁ ጥቂት ግለሰቦች መመዝበሩ በወጣቶች የሥራ እድል ፈጣራ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ያለው በመሆኑ እርምጃው ለወጣቶች የጎላ ጥቅም እንደሚኖረው ጠቅሷል፡፡ ወይዘሮ ወደርየለሽ ሞገስ የተባሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ድህነት ባለባት ሀገር ይህን ያህል ከፍተኛ ምዝበራ ይፈፀማል ብለው እንዳልጠበቁና ድርጊቱም እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎችን መያዝ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ተናግረው ህዝቡ በተለያዩ ችግሮች ተጠምዶ ግጭት ውስጥ  እንዲገባ ሲያደርጉት የነበሩት እነዚሁ ግለሰቦች ናቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የተፈፀሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የሃብት ምዝበራዎች የሚያሳዩት ይህንን ድርጊት ሊቆጣጠሩ የሚገባቸው ተቋማት ደካማነት የሚሳይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ከማል ሃሩን የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው " የተፈፀመው ወንጀል በተደራጀ ኃይል መንግስት የራሱ ህዝብ ዘረፈ የሚያስብሉ ናቸው" ብለዋል፡፡ የተፈፀሙት ወንጀሎች እንደ ሀገር ምን ያህል ውርደት ውስጥ የሚያስገባና የሚያሳፍር  መሆኑንና የተጀመረው እርምጃ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም