በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ህክምና ክፍል ጥበት ለተለያየ ችግር እየዳረገን ነው - ተገልጋዮች

53
ሶዶ ህዳር 5/2011 በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቲችንግና ሪፌራል ሆስፒታል የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ህክምና ማዕከል የሚስተዋለው የህክምና ክፍል ጥበት ለተለያዩ ችግሮች እየዳረጋቸው መሆኑን ተገልጋዮች ተናገሩ፡፡ ሆስፒታሉ በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል የማስፋፍያ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከዳሞት ወይዴ ወረዳ ነብሰ ጡር ልጃቸውን ለማሳከም የመጡት ወይዘሮ ወርቅነሽ ሳሮሬ በሚኖሩበት ወረዳ የበዴሳ ጤና ጣቢያ ሪፈር ጽፎለቸው ወደ ሆስፒታሉ እንደመጡ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡ የሆስፒታሉ ባሙያዎች ልጃቸው አልጋ ይዛ መታከም እንዳለባት ቢያሳውቋቸውም በህክምና ክፍል ጥበት ምክንያት ውጭ አንጥፈው እንዳስተኟት ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለነፋስ በመጋለጧ ጉዳት እንዳያጋጥማት መስጋታቸውን   ተናግረው ሆስፒታሉ የህክምና ክፍሉን ጥበት እንዲያስተካክል ጠይቀዋል፡፡ ለወሊድ በመቃረቤ የሃኪም የቅርብ ክትትል ያስፈልግሻል አልጋ መያዝ አለብሽ መባሏን የተናገረችው ወይዘሮ ሳራ አያኖ በሆስፒታሉ የሚስተዋለው የአልጋና የህክምና ክፍል እጥረት ከፍተኛ መሆኑን ገልጻለች፡፡ ህክምናዉን መከታተል ግድ ቢሆንም መሬት ላይ በተነጠፈ ፍራሽ ላይ ለመተኛት መገደዷንና ለነብሰ ጡር እናት ምቾት እንደሌለው ተናግራለች፡፡ ሆስፒታሉ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ህክምና ማዕከል ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨረሲቲ ጤና ሳይንስና ህክምና ኮሌጅ ኃላፊና የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ጌታሁን ሞላ ናቸው፡፡ አገልግሎቱን የሚፈልጉ ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ጥበቱ ሊገጥም መቻሉን ገልጸው ችግሩን ለመቅረፍ የተወሰዱ ጊዜያዊ መፍትሄዎችም በቂ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ ከክፍል ጥበት ጋር እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎች የተጀመረው የህንጻ ግንባታ ሲጠናቀቅ በዘላቂነት የሚፈታ ቢሆንም በአከባቢዉ የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ሸክሙን መጋራት እንዲችሉ ስልጠና በመስጠት በጋራ ለመስራት አቅጣጫ መያዙንም ገልጸዋል፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ፕሮጄክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ ሌንጫ በሆስፒታሉ በእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ህክምና ማዕከል አገልግሎቱን ፈላጊውና ክፍል አለመመጣጠኑን ገልጸዋል፡፡ ''ተገልጋዮቹ ያነሱት ቅሬታ ትክክል ነው በጊዜያዊነት ወለሉን በመስተዋትና በተለያዩ ቁሳቁሶች በመከፋፈል እንዲጠቀሙ ተደርገዋል'' ብለዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል ባለ ሶስት ፎቅ ህንጻ በግንባታ ሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ግንባታው አጎራባች ዞኖችንም ታሳቢ ያደረገና ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተናግረዋል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም