የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄች ለመመለስ በቁርጠኝነት እሰራለሁ-- ጋህአዴን

57
ጋምቤላ ጥቅምት 5/2011 የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ/ጋህአዴን/በየደረጃው በሚገኙ የአመራር አካላት ላይ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በማጥራት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄች ለመመለስ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታወቀ። ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ከ550 በላይ የአመራር አካላት የተሳተፉበት ግምገማ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምራል። የድርጀቱ ሊቀመንበር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ጋህአዴን በከፍተኛ አመራሩ የተጀመረውን ግምገማ በየደረጃው በሚገኙ የድርጅቱ አመራሮች ላይ አጠናክሮ በማስቀጠል ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየሰራ ነው። ድርጅቱ በቡድንተኝነት፣ በጎሰኝነት፣ በብሔረተኝነት፣ በኪራይ ሰብሳቢነትና ሌሎችም ብልሹ አሰራሮች ያሉባቸውን አመራሮች ለማጥራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በተጠቀሱት ችግሮች የተዘፈቁ አመራሮች በድርጅቱ ሊቀጥሉ እንዳማይችሉም ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል ። በድርጀቱ በማዕከላዊ ኮሚቴ የተጀመረውን ግምገማ ከክልል እስከ ወረዳ በሚገኙ አመራሮች ላይ መጀመሩን ገልጸዋል። ድርጅቱ እያካሄደ ባለው ጥልቅ ግምገማ አቅምና የጠራ ልማታዊ አስተሳሰብ  ያላቸውን አመራሮችን በመለየትና በማደራጃት በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ተናግረዋል። እንደ ሀገር የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ወደፊት ለማራመድ ጭምር ጋህአዴን በትኩረት እንደሚሰራ ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል። በጋምቤላ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ጥልቅ ግምገማ ከ550 በላይ  የክልል፣ የዞንና የወረደ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም