አምባሳደሮቹ በኢንቨስትመንት፣ በአቅም ግንባታና በበጎ አድራጎት ተግባራት ዙሪያ ውይይቶችን አካሂደዋል

52
አዲስ አበባ ህዳር 5/2011 በተለያዩ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ቆንስል ጄኔራል በኢንቨስትመንት፣ በአቅም ግንባታና ድጋፍ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን አካሂደዋል። በቻይና ጉዋንዡ የኢትዮጵያ ቆንስል ጀኔራል አቶ ተፈሪ መለሰ ከጉዋንዶንግ ግዛት ከተውጣጡ የተለያዩ ኩባንያዎች ጋር ተወያይተዋል። ቆንስል ጀኔራሉ የኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎች አብራርተው ኩባንያዎቹ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር፣ በቱሪዝምና በሌሎች መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበውላቸዋል። በቻይና የውጭ ኢንቨስትመንት ህብረት ምክትል ኃላፊ ማዲሰን ማ በበኩላቸው የማህበሩ አባል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማህበሩ ማበረታቻ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። የጉዋንዶንግ ግዛት ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል። በማሌዢያ፣ ሲንጋፓርና ኢንዶኔዢያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬም ከኢንዶኔዢያ የህዝብና የኩነቶች ምዝገባ ዳይሬክተር ጄኔራል ፕሮፌሰር ዙዳን ፋክሮሎህ ጋር ተወያይተዋል። አገራቱ በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ላይ መተባባር በሚችሉበት ሁኔታና በዘርፉ የአቅም ግንባታ፣ የቴክኒክ ድጋፍና ልምድ ልውውጥ ትብብር ለማድረግ መግባባት ላይም ደርሰዋል። በተጨማሪም አምባሳደሩ ከሜንሳ የኩባንያዎች ስብስብ ዋና ስራ አስኪያጅ ጋር ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ በመድሃኒት ቅመማ መስክ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል አብራርተዋል። ሜንሳ በኢንዶኔዢያ በጤና አጠባበቅና በሎጂስቲክስ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ስብስብ ነው። በተመሳሳይ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ተበጀ በርሄ ከአገሪቱ የበጎ አድራጎት ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ሰዒድ አብዱልጋህኒ ጋር መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ገልጿል። ምክትል ዳይሬክተሩ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎችን ለመገንባት ዝግጅት ማጠናቀቁንና በተለያዩ ክልሎችም የበጎ አድራጎት ተግባራትን ለማከናወን ማቀዱን አክለዋል። አምባሳደር ተበጀ በበኩላቸው ድርጅቱ በኢትዮጵያ ያከናወናቸውን በጎ ተግባራት አድንቀው በጅምር ላይ ያሉ የልማት ስራዎች እንዲጠናቀቁ ኤምባሲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠውላቸዋል። የሁለቱ አገራት ግንኙነት ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ባለሃብቶችም በኢትዮጵያ በግብርና፣ በቱሪዝምና በሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም