ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠየቁ

77
አዲስ አበባህዳር 5/2011 የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው "አቅም ስለሌለኝ መንግስት ጠበቃ ያቁምልኝ" በማለት ጠየቁ። በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በትናትናው ዕለት በቁጥጥር ስር የዋሉት የሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የመንግስትና የህዝብ ሃብትን በከፍተኛ ሁኔታ መመዝበር፣ ያለጨረታ ግዥ መፈጸም፣ የንብረቶች ብክነትና መጥፋት፣ የፕሮጀክቶች መጓተት እና ከሌሎች ጋር ጥቅም መጋራት ተጠርጥረው ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ይገኙበታል። ተጠርጣሪው ወርሃዊ ገቢያቸው በጡረታ የሚያገኙት አራት ሺህ ብር በመሆኑ ጠበቃ ለማቆም አቅም እንደሌላቸውና በመንግስት በኩል ጠበቃ እንዲቆምላቸው ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል። ከፍተኛ ሃብት በማካበትና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተያያዘ ወንጀል ተጠርጥረው የቀረቡት የቀድሞው የኢትዮቴሌኮም የስራ ኃላፊ ወንድማቸው አቶ ኢሳይያሳ ዳኘው በተመሳሳይ ጠበቃ የማቆም አቅም የለኝም በማለት መንግስት እንዲያቆምላቸው ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል። "አንድ መኖሪያ ቤት እንጂ ገቢ የሚያስገኝ ንብረት የለኝም፤ ደመወዜም ከስምንት ሺህ ብር በታች ነው" ብለዋል ለፍርድ ቤቱ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም