ከጉጂ ዞን በሀገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች እገዛ ላደረጉ አካላት ሽልማት ተሰጠ

79
ነገሌ ህዳር 5/2011 ከጉጂ ዞን  በሀገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ላመጡ  ተማሪዎች ፣ እገዛ ላደረጉ ባለሙያዎችና ባለድርሻዎች አካላት የእውቅናና የገንዘብ ሽልማት ተሰጠ፡፡ ሽልማቱ  ለላቀ  ስራ እንደሚያነሳሳቸው ተሸላሚ ተማሪዎችና መምህራን ገልጸዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም. በተሰጠው  ሀገር አቀፍና ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላመጡ 21 ተማሪዎች ከአንድ ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ብርና መጽሐፍት ሽልማት መበርከቱን  የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡ ሞዴል የፈጠራ ስራ ያከናወኑ ተማሪዎች፣ ሶስት መምህራንና 17 የተማሪ ወላጆች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የአንዳንድ ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። በትምህርት አሰጣጥ፣ በመልካም ስነ ምግባርና ለትምህርት ስራ ባበረከቱት በጎ ተግባር ሞዴል በመሆን ለተመረጡ ስድስት ትምህርት ቤቶችና  ሶስት የወረዳ አስተዳዳሪዎች የኮምፒውተር ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ሽልማቱን ትናንት የሰጡት የጉጂ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሮባ ተርጫ "የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ባልተሟላበት ሁኔታ በመደበኛ ትምህርት  የተመዘገበው የተማሪዎች ውጤት የሚያኮራ ነው "ብለዋል፡፡ በብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት ለከፍተኛ የትምህርት ደረጃ የበቁ ተማሪዎች ለተሻለ ውጤት በርትተው እንዲያጠኑ መክረዋል፡፡ ውጤታማ ስራ ያከናወኑ የትምህርት ባለድርሻ አካላትን ያመሰገኑት አስተዳዳሪው በየዓመቱ የሚሰጠው  እውቅና ና የማበረታቻ  ሽልማት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ በኡራጋ ወረዳ በሀገር አቀፉ ፈተና 600 ነጥብ በማምጣት 10 ሺህ ብር የተሸለመው ተማሪ ያደሳ ብርሀኑ "ድጋፍና ትብብር ላደረጉልኝ ለመንግስት፣ ለመምህራንና ለወላጆቼ ምስጋና አቀርባለሁ" ብሏል፡፡ ሽልማቱ ጠንክሮ ለመማርና የተሻለ ውጤት ለማምጣት መነሳሳት እንደፈጠረለት ገልጿል፡፡ ዜጋን በእውቀትና በስነ ምግባር ቀርጾ ለውጤት ማብቃት የመምህራን ግዴታ ቢሆንም እውቅናና ሽልማት መሰጠቱ ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ እንደሆነ በዞኑ የኡራ ወረዳ የሂሳብ መምህር ኃይሉ አበበ ገልጸዋል፡፡ በሂሳብ መምህርነት ሙያ ሞዴል ሆነው በመመረጥ በተበረከተላቸው የገንዘብ ሽልማትና እውቅና መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ በሽልማቱ 23 ተማሪዎች፣ ሶስት ሞዴል መምህራን፣17 የተማሪ ወላጆች፣ ስድስት ትምህርት ቤቶችና ሶስት ወረዳዎች መካተታቸው ታውቋል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም