በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆኑ

85
መተማ ግንቦት 15/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን ገጠራማ አካባቢዎች ዘንድሮ በተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ የግብርና ልማት መምሪያ አስታወቀ። ተጠቃሚዎች በበኩላቸው የውሃ ተቋማት በአቅራቢያቸው በመገንባቱ ጊዜና ጉልበታቸውን እንደቆጠበላቸው ተናገሩ። በመምሪያው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ዋና የሥራ ሂደት መሪ አቶ ካሳ አሰጌ ለኢዜአ እንደገለጹት በገጠራማ አካካቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው። በተያዘው በጀት ዓመት ከ30ሺህ በላይ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቀሚ ማድረግ የተቻለው 20 የእጅ ጉድጓድና ሦስት የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ፕሮጅክቶች ተገንብተው በመጠናቀቃቸው መሆኑንም ገልጸዋል። በገጠር ከተገነቡት የውሃ ፕሮጅክቶች በተጨማሪ በመተማ ወረዳ ኮኪት ከተማ ተጨማሪ የውሃ ተቋም እንዲገነባ መደረጉን አቶ ካሳ ተናግረዋል፡፡ የውሃ ተቋማቱን ለመገንባት ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች 34 ሚሊዮን ብር  ድጋፍ  መደረጉንና ሕብረተሰቡም በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በጉልበት ካደረገው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ከ300 ሺህ ብር በላይ ማዋጣቱን ተናግረዋል። እንደ አቶ ካሳ ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅትም 30 የእጅ ጉድጓዶችና አራት የጥልቅ ጉድጓድ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የእጅ ጉድጓዶቹ እስከ ነሀሴ ወር አጋማሽ ድረስ ተጠናቀው ለአገልግሎት ይበቃሉ። የጥልቅ ጉድጓድ ፕሮጀክቶቹም በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ሩብ ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው አቶ ካሳ ያስታወቁት። "ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት የውሃ ፕሮጀክቶች የዞኑን የውሃ ሽፋን ከ70 ወደ 74 በመቶ ማሳደግ የቻሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁም ሽፋኑ ወደ 81 በመቶ ከፍይላል" ብለዋል። በዞኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በመተማ ወረዳ ላስታ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገብሩ ጥሩነህ እንዳሉት ቀደም ሲል የመጠጥ ውሃ በአህያ ጭኖ ለማምጣት ከ3 እስከ 4 ሰዓት ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል። በእዚህም ንጽህናው ያልተጠበቀ የወንዝ ውሃ በመጠቀም ለተለያዩ የውሃ ወለድ በሽታዎች ሲጋለጡ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት የውሃ ተቋማቱ መገንባታቸው ይህን ችግራቸውን ይፈታል የሚል አምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አለምሰገድ ሽፈራው በበኩላቸው የመጠጥ  ውሃ ከወንዝ ለማስቀዳት ልጃቸውን ከትምህርት ቤት የሚያስቀሩበት አጋጣሚ እንደነበር አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት በአቅራቢያቸው የውሃ ተቋም መገንባቱ ንጽህናው የተጠበቀ ውሃ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ ልጃቸው ትምህርቱን በአግባቡ ለመከታተል እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። በኮኪት ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ ሰናይት አማረ በበኩላቸው በከተማዋ የጋራ ቦኖ ውሃ ተጠቃሚ እንደነበሩ ጠቁመው፣አሁን  ከጥልቅ ጉድጓዱ  ቤታቸው ድረስ  ቧንቧ  በመግባቱ ለወረፋ ጥበቃ ያባክኑት የነበረው ጊዜ መቆጠቡን ገልጸዋል። በእዚሁ ከተማ የሚኖሩት አቶ ቢሰጥ አድኖ በበኩላቸው በቤታቸው የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸው እንዳስደሰታቸውና ለውጡ ለከተማዋ እድገት አንድ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም