በደቡብ ክልል በህጻናት ላይ የሚፈጸመውን የጉልበት ብዝበዛ ለማስቆም በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

75
ሀዋሳ ህዳር 5/2011 በደቡብ ክልል በህጻናት ላይ የሚፈጸመውን የጉልበት ብዝበዛ፣ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቆም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ አስታወቀ፡፡ በመጪው ቅዳሜ የሚከበረውን አለም አቀፍ የህጻናት ቀን አስመልክቶ የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በክልሉ በህጻናት ላይ የሚፈጸመው የጉልበት ብዝበዛ ለማስቀረት  የክልሉ ነዋሪዎች በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል፡፡ ከክልሉ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ህገወጥ የህጻናት ዝውውር እንደሚካሄድ የጠቆሙት ኃላፊዋ ይህን ህገወጥ ዝውውር ለማስቀረት ቢሮው ከፍትህ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ህገወጥ ዝውውሩ በተለያዩ የስራ መስኮች ህጻናትን በማሰማራት ለግል ጥቅማቸው ለማዋል በሚሯሯጡ ግለሰቦች እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡ በየአካባቢው ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን በመከታተል ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ከህገወጥ የህጻናት ዝውውርና የጉልበት ብዝበዛ ጋር ተያይዞ በተወሰኑ አካባቢዎች በህግ ከተቀመጠው አንጻር በተገቢው መንገድ ባለመሰራቱ ድርጊቱ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ይህን ችግር በዘላቂነት ለማስቆም ቢሮው ከፍትህ አካላት ጋር ያለውን የቅንጅት አሰራር በተያዘው ዓመት አጠናክሮ በመቀጠል ለለውጥ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭትና ሁከት ተከትሎ በርካታ ሴቶችና ህጻናት ተጎጂ መሆናቸውን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊዋ ህብረተሰቡ እነዚህን ህጻናትና ሴቶች በመደገፍ እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በመጪው ቅዳሜ የሚከበረውን አለም አቀፍ የህጻናት ቀን አስመልክቶም በክልሉ አምስት ከተሞች በህጻናት ላይ ያተኮረ ፊልም እየታየ እንደሚገኝና ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህር እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡ በበዓሉ ላይ 100 ለሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ሴቶችና ህጻናት የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል፡፡ በዓሉ ’’ፍቅር ተስፋ ጥበቃ ለሁሉም ህጻናት’’ በሚል መሪ ሀሳብ በክልል ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም