የመዲናዋ ተቋማት የደህንነት መስፈርት እንዲያሟሉ ህግ እየተዘጋጀ ነው

58
አዲስ አበባ ህዳር 5/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ተቋማት የደህንነት መስፈርት እንዲያሟሉ የሚያደርግ ህግ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለፀ። የከተማዋ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቤቶ ዲማ ለኢዜአ እንዳሉት ባለስልጣኑ አደጋዎች እንዳይደርሱ ለመከላከል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ተቋማት የደህንነት መስፈርት ማሟላታቸውን ለማረጋገጥ በባለስልጣኑ የሚደረገው ፍተሻና የሚሰጠው የሙያ ምክርም ከቅድመ አደጋ መከላከል ተግባራት ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል። ባለስልጣኑ የሚሰጠውን የሙያ ምክርና ግብረ-መልስ ተቋማት ከመስማት በዘለለ እየተገበሩት አለመሆኑን የተናገሩት አቶ ቤቶ ይህን ችግር ለመቅረፍ የፍተሻ ስራውን በህግ የተደገፈ ለማድረግ "ፋየር ኮድ" እየተዘጋጀ ነው ብለዋል። የከተማዋ ፍትህ ቢሮ በህጉ ላይ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጥ እየታየ መሆኑንና በቅርቡም ለከተማዋ ካቢኔ እንደሚቀርብ ነው ያብራሩት። ህጉ ተቋማት የደህንነት መስፈርት እንዲያሟሉና የብቃት ማረጋገጫ እንዲኖራቸው የሚያስገድድ እንደሚሆንም ተናግረዋል። የባለድርሻ አካላትን ተግባራት ያካተተ መሆኑን ገልጸው ይህም የሚስተዋሉ የቅንጅት ችግሮችን ለመፍታትና አደጋን ለመከላከልና ለመቀነስ ያስችላል ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም