በምዕራብ ኦሮሚያ የሚታየውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

77
ነቀምቴ ህዳር 4/2011 በምዕራብ ኦሮሚያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ከመንግሥት ጎን ሆነው የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ በነቀምቴ ከተማ ዛሬ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄዷል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ፓስተር ተስፋዬ ሃይሌ በሰጡት አስተያየት በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ምስራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው ለመመለስ በሚያደረገው ጥረት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከመንግሥት ጎን በመቆም የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ወደ ነበረበት ለመመለስ መንግሥት ለሚያደርገው ጥረት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የባህልና የሥነ ልሣን መምህር ዶክተር ፍሌ ጃራ በበኩላቸው  መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄ አፋጣኝ  ምላሽ በመስጠት የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በሚያደረገው ጥረትም የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ከመንግሥት ጎን በመቆም የሚፈለግባቸውን የዜግነት ግዴታ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ሁሉም በፈለገበት ሰዓት ተነስቶ መንገድና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መዝጋት በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ዶክተር ፍሌ ጃራ ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን መካነ ኢየሱስ ማዕከላዊ ሲኖዶስ የነቀምቴ ክርስቲያን ማሰልጠኛ ኮሌጅ መምህር ቄስ አስፋው ተርፋሳ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የራሱንና የአከባቢውን ሰላም መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኘው አክትቪስት ጃዋር መሐመድ በበኩሉ ህብረተሰቡ በየደረጃው ከሚገኙ አመራር አካላት ጋር በመሆን በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ማስቀጠል እንዳለበት አሳስቧል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው የክልሉ ሕዝብና ወጣቶች በአገሪቱ የመጣው ለውጥ ለማስቀጠል ከክልሉ መንግስት ጋር መተባበር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ መንግሥትም ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ/ ጋር የጀመረውን ውይይት በማጠናከር ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም