''መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰደ ያለው እርምጃ አገራዊ ለውጡን ለማፋጠን ያስችላል''-የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች

54
ድሬዳዋ ጥቅምት 4/2011 መንግሥት በሌቦችና አጥፊዎች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ባለፈ አገራዊ ለውጡን እንደሚያፋጥን የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች እንደተናገሩት መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት የጀመረው እንቅስቃሴ አገራዊ ለውጡን በሚያፋጥን መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። እርምጃው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በመሸጉት አጥፊዎችና ሌቦች ጭምር እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡ የሳቢያን ትምህርት ቤት መምህርት መርሻዬ ባዩ ለዘመናት የሀገሪቱን እንጡራ ሃብትና ንብረት የሰረቁና ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ ሌቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ የሕዝቡን የዓመታት ጥያቄ የመለሰና ያስደሰተ ተግባር ነው ብለውታል፡፡ ዜጎችም ከመንግሥት ጎን በመቆም አጥፊዎችን በማጋለጥ ሀገራዊ ለውጡን ከዳር ማድረስ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ የገንደቆሬ ሠፈር ነዋሪ አቶ ሐሰን ዑመር መንግሥት በብረታ ብረት ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን አመራሮች ላይ መውሰድ የጀመረው እርምጃ መጠናከር እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ ''እርምጃው ማንም ወንጀል ሰርቶና  ሰብዓዊ ጥፋትን ፈፅሞ ተሸሽጎ የማይቀር መሆኑን አሳይቶናል።ይህ የሚያስደስትና የሚያረካ እርምጃ እንዲጠናከር ኃላፊነቴን  እወጣለሁ'' ብለዋል፡፡ እርምጃው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ መንግሥት ላይ የነበረኝን ጥርጣሬ የገፈፈና ለውጡ እንደማይቀለበስ ያረጋገጠልኝ ነው ያለው ወጣት ዘመድኩን ደሳለኝ ነው፡፡ ''የሕግ የበላይነት የማረጋገጡ ተግባርና ሌቦችን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ በየደረጃው በሚገኙ አጥፊዎች ላይ መቀጠል አለበት'' ሲልም ሐሳቡን ሰጥቷል፡፡ ሌላው ወጣት አብዱልአዚዝ መሐመድ መንግሥት ለፍቅር፣ለይቅርታና ለመደመር ከሰጠው ትኩረት ጎን ለጎን አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረቡ ዜጎች ለለውጡ ስኬት እንዲተጉ  ያደርጋል ብሏል፡፡ እርምጃውን በመንግሥት ላይ ያላቸውን ተስፋ  እንዳጠናከረላቸው የሚናገሩት ደግሞ የለገሀሬ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ሳፊያ ሙሜ ናቸው፡፡ ‹‹መንግሥት በወታደራዊ ተቋም መውሰድ የጀመረውን እርምጃ በሲቪል አጥፊ ባለሥልጣን ላይ በመድገም የሕግ የበላይነትን  ማረጋገጥና እርምጃውን ሙሉ ማድረግ  አለበት'' ብለዋል፡፡ አቶ ገብሬ አበራ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው እርምጃው በመላ አገሪቱ  መቀጠልና አገራዊ ለውጡን ለማሳካት ተባብረው መሥራት እንደሚያስፈለግ ተናግረዋል፡፡ የመልካ ጀብዱ ነዋሪ አቶ መላኩ ታደሰ መንግሥት በጥበብ ፣ በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመስርቶ መውሰድ የጀመረው እርምጃ አስደሳች መሆኑን ይገልጻሉ።የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ዜጎች በለውጡና በመንግሥት ላይ እምነት እንደሚያሳድርባቸው ገልጸዋል፡፡ ''መንግሥት ጥፍር አወጣ። ይህ ጥፍር ስለቱን ጠብቆ እስከ ድሬደዋ መዝለቅ አለበት'' ሲሉም  እርምጃው እንዲቀጥል ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ እርምጃውበሁሉም መስኮች እንዲሳካ የሕዝብ ትብብርና ድጋፍ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ እስክንድር ባሻ የተባሉ ነዋሪ ናቸው። የሕዝብን ሃብትና ንብረት የዘረፉና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ቅጣት እንዲያገኙ አጥፊዎችን አጋልጦ በመስጠት ዜጎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም