በኢትዮጵያ የስኳር ህመም ስርጭት አስጊ ሆኗል።

100
አዲስ አበባ ኅዳር 4/2011 በኢትዮጵያ የስኳር ህመም ስርጭት አስጊ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ አዲስ አበባ ኅዳር 4/2011 የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ነገ በዓለም አቀፍና በኢትዮጵያ ለ28ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የስኳር ህመም ቀን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። ቀኑ  ቤተሰብ የስኳር ህመምን ለመከላከል  ባለው ሚና ላይ ተመስርቶና  "የስኳር ህመም ይመለከተኛል" በሚል መሪ ሀሳብ በብሔራዊ ትያትር ይከበራል። የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዱራዛቅ አህመድ በኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ከስኳር ህመም ጋር እንደሚኖሩ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የስኳር ህመም ስሜትና ምልክት ሳይታይ የጤና ምርመራ የማድረግ ባህል አነስተኛ በመሆኑ ከስኳር ህመም ጋር እየተኖረ እንኳን ማወቅ ባለመቻሉ የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚያጎላው ተናግረዋል። በህመሙ ከተያዙት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች በተጨማሪ ሌሎች 9 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች በተለያየ አጋጣሚ የስኳር መጠን መዛባት እየጋጠማቸው መሆኑንና ይህም ችግር ካልተፈታ የታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር እንደሚችል አመልክተዋል። በአብዛኛው በኢትዮጵያ በስኳር ህመም የሚኖሩ ሰዎች በምርመራ የጤና ሁኔታቸውን ያላወቁ መሆናቸውን ነው ዶክተር አብዱራዛቅ ያስረዱት። አሁን ባለው ሁኔታ የስኳር ህመም ስርጭት በቁጥጥር ስር ካልዋለ ህመሙ ልብን፣ ዓይንን፣ ኩላሊቶችን፣ ነርቮችንና የደም ቱቦዎችን ተግባር በመጉዳትና ተግባራቸውን በማስተጓጎል ከባድ የጤና ቀውስ እንደሚያስከትልም ጠቅሰዋል። ማህበሩ የህመም ስርጭቱን አሳሳቢነት በመገንዘብ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ፣ የመድሐኒት አቅርቦትና የህክምና ተደራሽነቱን ለማስፋትና ለጤና ባለሙያዎች ሙያዊ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ጤናማ ያልሆነ የአኗኗርና የአመጋገብ ዘይቤ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መቀነስ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረትና የደም ግፊት ለስኳር ህመም አጋላጭ ሁኔታዎች እንደሆኑም ነው ዶክተር አብዱራዛቅ ያስረዱት። በአጠቃላይ የስኳር ህመምን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ መከተል በተለይ ሁለተኛውን የስኳር አይነት በ80 በመቶ ለመከላከል እንደሚያስችል ጠቅሰዋል። ህብረተሰቡ በተቻለው አቅም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር እንደሚገባውና አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ እንዲሁም ህመም ቢሰማም ባይሰማም በዓመት አንድ ጊዜ የስኳር ህመም ምርመራ ማድረግ እንደሚገባውም ምክራቸውን አቅርበዋል።  የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ባለሙያ አቶ አፈንዲ ኡስማን በበኩላቸው ሚኒስቴሩ አሁን ያለውን የስኳር ህመም ችግር አሳሳቢነት ለመከላከል የሚያስችሉ ጅምር ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል። የስኳር ህመም መርሃ ግብር ከፌደራል እስከ ክልል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል እንደ ዋና መርሃ ግብር በማካተት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ የአምስት ዓመት አገር አቀፍ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ አቅድ የስኳር ህመምን በዋናነት ባከተተ መልኩ አዘጋጅቶ የመተግበር ስራንም እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎችን፣ የጤና ማህበራትንና የባለድርሻ አካላትን ያካተተ ብሔራዊ የስኳር ህመም መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ ግብረ ሃይልም ተቋቁሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው አቶ አፈንዲ ያስረዱት። በተጨማሪም የስኳር ህመም መድሃኒቶች ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ እንዲገኝ ለማድረግም ሁኔታዎችን የማመቻቸት፣ በተቀናጀ መልኩ የስኳር ህመምን ለመከላከል በጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች  የበሽታውን የመቆጣጠር መርሃ ግብር ስራዎችና ሌሎችም ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል። የስኳር ህመምን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካል አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ዓለም አቀፉ የስኳር ህሙማን ቀን ነገ በብሔራዊ ትያትር ሲከበር የፓናል ውይይት እንደሚካሄድና የህክምና ባለሙያዎችም ስለ በሽታው ገለጻ እንደሚያደርጉ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተጠቅሷል። የስኳር ህመም የሚከሰተው ሰውነታችን ለኑሮም ሆነ ለእድገት የሚያስፈልገውን ስኳር በትክክል ለመጠቀም ሳይችል ሲቀር ሲሆን አንድ ሰው የስኳር ህመም አለው የምንለው በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ ሲገኝ እንደሆነም የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ። እንደ ዓለም አቀፉ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን መረጃ መሰረት በዓለም ደረጃ ከ420 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከህመሙ ጋር የሚኖሩ ሲሆን አስፈላጊው የበሽታው መከላከልና መቆጣጠር ካልተሰራ እ.አ.አ በ2020 የህሙማኑ ቁጥር በእጥፍ ሊጨመር እንደሚችልም ግምቱን አስቀምጧል። የያዝነው ህዳር ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ህመም የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር በሚል ተሰይሟል። በኢትዮጵያ በበሽታው ከተያዙ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 90 በመቶው በሁለተኛው የስኳር አይነት የተያዙ ሲሆን የተቀሩት በአንደኛው የስኳር አይነት የተያዙ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም