ኔዘርላንድስ ለልብ ህክምና ማዕከል ማቋቋሚያ የገንዘብ ድጋፍ አደረገች

65
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 ኔዘርላንድስ በኢትዮጵያ የልብ ህክምና ማዕከል ለማቋቋም የሚውል የ632 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች። በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ አምባሳደር ሚስተር ቢ ቫን ሎስድሬችት እና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ የድጋፍ ስምምነቱን ተፈራርመዋል። ሚስተር ቢ ቫን ሎስድሬችት በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለሚቋቋመው የልብ ህክምና ማዕከል መንግስታቸው 19 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 632 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ድጋፍ በማድረጉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል። በአጠቃላይ ለልብ ህክምና ማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው ወጪ 39 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን ቀሪው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው። የልብ ማዕከሉ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ እና የህክምና መሳሪያ ተሟልቶለት በልብ ህመም የሚሰቃዩ ኢትዮጵያዊያን ሲፈወሱ ማየት ምኞታቸው መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል። ለልብ ህክምና ማዕከሉ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በህክምና መሳሪያዎች አምራችነቱ በሚታወቀው ፊሊፕስ ኩባንያ እንደሚሟላ ነው አምባሳደሩ የተናገሩት። የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ዩኒቨርስቲ በልብ ህክምና ባለሙያዎችን ለማሰልጠን የሚወጣውን ወጪ ጨምሮ ለማዕከሉ ግንባታ የኔዘርላንድስ መንግስት ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ ምስጋናቸው አቅርበዋል። ማዕከሉ በመጪው ነሐሴ ግንባታው ተጀምሮ በሁለት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ነው የገለጹት። የልብ ህክምና ማዕከሉ 94 አልጋዎች፣ አራት የቀዶ ጥገና ህክምና ክፍሎች እንደሚኖሩትና በወር 500 ቀዶ ህክምና የማከናወን አቅም እንዳለው ተናግረዋል። የጥቁር አንበሳ የልብ ህክምና ማዕከል ከህክምና አገልግሎቱ ባሻገር የሰው ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል በመሆን ትልቅ አቅም የሚፈጠርበት ይሆናል ብለዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በመቐሌ ዓይደር፣ በጎንደርና በጅማ ሆስፒታሎች የልብ ህክምና ማዕከላት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በአገሪቱ ያሉ ሪፈራል ሆስፒታሎች ልዩ የከፍተኛ የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸው ፍኖተ-ካርታ እየወጣላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም