ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን ለህዋ ሳይንስ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተጠቆመ

107
መቀሌ ህዳር 4/2011 የሀገሪቱ ልማት ቀጣይነት እንዲኖረው ከፍትኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን ለህዋ ሳይንስ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ማህበር በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ ተማሪዎችና መምህራን ትናንት በዘርፉ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ቤዛ ተስፋዬ እንደገለጸችው ህዋ ሳይንስ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች ለመጠቀም የጎላ ድርሻ አለው፡፡ በከርሰ ምድር ያለውን ሃብት ለማወቅና ለልማት ጥቅም ላይ ለማዋል የህዋ ሳይንስ ትምህርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የገለጸችው፡፡ " ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግና ሀገራዊ ልማቱን ለማስቀጠል ከፍትኛ የትምህርት ተቋማት የህዋ ሳይንስን በምርምርና በጥናት መደገፍ ይኖርባቸዋል " ብላለች። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ሳይንስ ቀመር ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሃፍቱ አለማዮሁ በበኩላቸው የህዋ ሳይንስ በሳተላይት የሚደረጉ ግንኙነቶችን ለማጎልበት ፋይዳው የጎላ መሆኑ ነው ያስረዱት። "የህዋ ሳይንስ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች መካከል ሰዎች በመሬት ላይ የሚፈልጉትን እንዲያውቁ ከማድረግ ባለፈ ለአየር ንብረት ትንበያ ቅድመ ትንታኔ ለመስጠትና ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ይረዳል" ብለዋል፡፡ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲም ህዋ ሳይንስ ለሀገር ልማት ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ዶክተር ሀፍቱ ተናግረዋል። ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል የሶፍትዌር ኢንጂነሪን ሦስተኛ ዓመት ተማሪና የኢትዮጵያ ህዋ ሳንይስ ማህበር አባል የሆነው ትናኤል ሰርፀ በበኩሉ ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት በህዋ ሳይንስ ላይ ፕሮጀክቶች ሲሰሩ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ በዩኒቨርሲቲው የፊዚክዝ ትምህርት ክፍል ተማሪዎችና መምህራን የተገኙ ሲሆን ስለህዋ ሳይንስ ጠቀሜታና የማህበሩን እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ ማብራሪያ ተሰጥቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም