በደቡብ ክልል የአሜሪካ መጤ ተምችን የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል .... አቶ ደሴ ዳልኬ

75
ሀዋሳ ግንቦት 15/9/2010 በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን በበልግ እርሻ በአገዳ ሰብሎች ላይ የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች ለመከላከል የተሰራው ሥራ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ ዳልኬ በዞኑ ቦርቻ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች በአገዳ ሰብሎች የተሸፈነ ማሳን ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት አርሶ አደሩ ተምቹን ለመከላከል በተለያዩ አደረጃጀቶቹ እያከናወነ ያለው ተግባር ተምቹ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር አስችሏል፡፡ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም አካባቢዎች ተምቹ መከሰቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ከኬሚካል ይልቅ በእጅ ለቀማ ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት ውጤታማ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሲዳማ ዞን በአገዳ ሰብሎች በተሸፈነ ማሳ ላይ የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች ለመከላከል እየተደረገ ያለው ሥራ ውጤታማ በመሆኑ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ተምቹን በዘለቄታ ለመከላከል እንዲቻል የጥናትና ምርምር ተቋማት ዘላቂ መፍትሄ በምርምር ማምጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ የበልጉ ዝናብ በጥሩ ሁኔታ ሲጥል በነበረበት በመጀመሪያዎቹ ወራት የተምቹ ክስተት ጎልቶ ባለመታየቱ መዘናጋት ፈጥኖ እንደነበር ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ዝናቡ ከቀነሰበት ጊዜ አንስቶ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ ተምቹ መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በበልግ እርሻው በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በአገዳ ሰብሎች መልማቱን ገልጸዋል። በአገዳ ሰብሎች ከለማው ሰብል በ12 ሺህ ሄክታሩ ላይ የአሜሪካ መጤ ተምች ቢከሰትም ተምቹ ጉዳት ሳያደርስ በለቀማና በኬሚካል ርጭት ለመከላከል መቻሉን አስረድተዋል፡፡ በክልሉ በዘንድሮ ዓመት የእርሻ ሥራ ለሰብል ጥበቃ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ስምምነት በማድረግ ነው ወደሥራ የተገባው። አምና በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ሰብል ሲያጠቃ የነበረው አሜሪካ መጤ ተምች በአገዳ ሰብሎች ላይ በተለይ በበቆሎና በማሽላ ላይ እንደሚከሰት በመለየቱ አስቀድሞ የቁጥጥር ሥራ መስራቱን ጠቁመዋል፡፡ ተምቹ በተከሰተባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ በአስር ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ በለቀማ ተምቹን የመከላከል ሥራ አከናውኗል። በቀሪው 2 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይም በለቀማና በኬሚካል ተምቹን የመከላከል ሥራ የተሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ተምቹን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን አቶ ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ አዱላ በበኩላቸው አሜሪካ መጤ ተምች አምና በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በበቆሎ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰው ዘንድሮ ተምቹ በበቆሎ ማሳ ላይ ቢከሰትም ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ በህዝብ በተደራጀ ንቅናቄ ተምቹን መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን ለአመራሩና ለአርሶ አደሩ የተሰጠው የግንዛቤ ስልጠናም አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ በበቆሎ ከተሸፈነው 51 ሺህ ሄክታር ማሳ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ ከተምች ክስተቱ ጋር በተያያዘ የምርት መቀነስ ችግር ይገጥማል የሚል ስጋት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ በሲዳማ ዞን ቦርቻ ወረዳ ሀንጃጎሮ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር እስራኤል ቱምቻ እንዳሉት ዘንድሮ የበልጉ ዝናብ ለበቆሎ፣ ቦሎቄና ድንች ማሳቸው አመቺ በመሆኑ ሰብሉ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ተምቹ በማሳቸው ላይ ቢከሰትም ቤተሰቦቻቸውን አስተባብረው ባከናወኑት የመከላከል ሥራ በሰብሉ ላይ ጉዳት ሳይደርስ ለመከላከል  መቻላቸውን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት ተምቹ በአካባቢያቸው በስፋት ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ፣ በወቅቱ በኬሚካል ለመከላከል ያደረጉት ሙከራ ብዙ ውጤታማ ባለመሆኑ ተምቹን በእጅ በመልቀም መጨረሳቸውን አመልክተዋል። በዝናብ እጥረትና በተምቹ ክስተት ምክንያት 50 ኩንታል ምርት ብቻ ማግኘታቸውን የጠቆሙት አርሶአደሩ፣ ዘንድሮ የዝናቡ ሁኔታም የተስተካከል በመሆኑ እስከ 65 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም