መንገዶች በግንባታ ቁሳቁስ በመዘጋታቸው ለእንቅስቃሴ እየተቸገርን ነው-....በመቀሌ እግረኞችና አሽከርካሪዎች

94
መቀሌ ህዳር 3/2011 መንገዶች በግንባታ ቁሳቁስና ተረፈ ምርቶች በመዘጋታቸው ለእንቅስቃሴ እየተቸገርን ነው ሲሉ በመቀሌ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ እግረኞችና አሽከርካሪዎች ገለፁ። የግንባታ ህግና ስርዓት ባልተከተሉ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል። በከተማው የሀወልት ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ በየነ ይልማ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የከተማው የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለግንባታ በሚቀርቡ አሸዋ፣ ጠጠር፣ ድንጋይና ብረታ ብረት እየተዘጋ ለእንቅስቃሴ አዳጋች ሆነዋል። ግንባታ ከሚካሄድባቸው ቦታዎች በቁፋሮ የሚወጣ አፈርና ፍርሰራሽም ለረዠም ጊዜ በመንገዶች ላይ ተቀምጦ ስለማይነሳ ለችግሩ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ነው የጠቆሙት ። በከተማው ጽዳናት ውበት ላይም ለአሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩን ተናግራዋል ። " በመንገዶች ላይ የሚቀመጥ  የግንባታ ቁሳቁስ የተሽከርካሪ እንቅሰቃሴ እንዲስተጓጎል ምክንያት እየሆነ ነው " ያለው ደግሞ የባለሶስት እግር ታክሲ አሽከርካሪ ወጣት አሸናፊ አለኝ ነው። የአፈርና የቁሳቁስ ክምር በወቅቱ አለመነሳትም የመንገድ ብልሽት እያስከተለ መሆኑን ተናግሯል። የመቀሌ ከተማ ፅዳትና ውበት ፅህፈት ቤት ኅላፊ አቶ ገብረሚካኤል እኑን "በዘርፉ የሚታየው ችግር የከተማውን ገፅታ እያበላሸው ነው" ብለዋል ። መንገዶች በግንባታ ቁሳቁስና ፍርስራሽ እየተዘጉ የፅዳትና ውበት ሥራው እንዲስተጓጎል ምክንያት መሆናቸውንም ተናግረዋል። የከተማው አስተዳደር ሕንፃ ሹም አቶ ክንፈ ግርማይ በበኩላቸው ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ቅሬታው ትክክል መሆኑን አምነዋል ። የግንባታ ህግና ስርዓት ባልተከተሉ ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቁመው ተደጋጋሚ ምክር ተሰጥቷቸው ተግባራዊ ያላደረጉ 860 ግለሰቦችና ተቋማት በማስጠንቀቂያና በገንዘብ መቀጣታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ። በከተማ አስተዳደሩ የመሰረተ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ሃፍቱ መብራህቱ " የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የመጠጥ ውሃ፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና መንገዶች ባለስልጣን ተቋማት ተቀናጅተውና ተናበው አለመስራት በትራፊክ እንቅስቃሴው እየታየ ላለው ችግር ሌላ ምክንያት ነው " ብለዋል ። እንደ ኃላፊው ገለጻ በተቋማቱ መካከል የሚታየውን የቅንጅት ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም