የመንገድ ዳር መብራት ባለመኖሩ በምሽት ዝርፊያ እየደረሰብን ነው----የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች

66
ሰቆጣ ህዳር 3/2011 በአካባቢያችን የመንገድ ዳር መብራት ባለመኖሩ በምሽት ዝርፊያ እየደረሰብን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ። የተቋረጠውን የመንገድ ዳር መብራት አገልግሎት ለማስጀመር ባጀት መመደቡን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል ። የከተማው  ነዋሪ ቄስ ሞገስ ደመቀ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማው  የመንገድ ዳር መብራት ባለመኖሩ ግለሰቦች ጨለማን ተገን አድርገው ጉዳት እያደረሱባቸው ነው። ባለፈው መስከረም ወር ውስጥ ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ዝርፊያና ድብደባ እንደደረሰባቸውም በማሳያነት ጠቅሰዋል። “በምኖርበት አካባቢ የመንገድ ዳር መብራት አገልግሎት ከተቋረጠ ስምንት ወር ሆኖታል “ ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ካሳወይ ጣሰው ናቸው፡፡ በቅርቡም በሌሊት ወደ መናኸሪያ በመሄድ ላይ እንዳሉ ድብደባና የንብረት ዝርፊያ የተፈፀመባቸው መሆኑን ነው የገለጹት። ሌላዋ የከተማው  ነዋሪ ወይዘሮ ተመኙ መንግስቴ በበኩላቸው ባካባቢያቸው የመንገድ ዳር መብራት ባለመኖሩ በጨለማ ወቅት ወጥተው ለመግባት ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ የከተማው ፖሊስ ፅህፈት ቤት የወንጀል መከላከል ተወካይ ሳጅን ሙሉቀን አስማረ "የመንገድ ዳር መብራቶች አገልግሎት ባለመስጠታቸው የወንጀል መከላከል ስራን  አስቸጋሪ  አድርጎታል" ብለዋል፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ጨለማን ተገን በማድረግ 23 የድብደባ፣ የዝርፊያና  ቤት ሰብሮ በመግባት የስርቆት ወንጀሎች መፈፀማቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ። የከተማው አገልግሎት ፅህፈት ቤት ችግሩን እንዲያውቅ ቢደረግም መፍትሄ ለአመገኘቱን ተናግረዋል። በኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የሰሜን ምስራቅ ሪጅን የሰቆጣ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪሮስ ፈረደ በበኩላቸው በከተማው በዋናና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ዳር የተዘረጉ መብራቶች ከረዥም ጊዜ አገልግሎት የተነሳ መበላሸታቸውን ተናግረዋል ። ዲስትሪክቱ ለጥገና የሚውሉ እቃዎችን የከተማ አስተዳደሩ ገዝቶ አንዲያቀርብ በነሃሴ 2010 ዓ.ም በደብዳቤ ቢያሳውቅም ምላሽ ባለመገኘቱ ችግሩ እስካሁን መቀጠሉን ገልጸዋል ። የከተማው  አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥጋቡ ሽመልስ  ከዲስትሪክቱ በቀረበ የእቃ ዝርዝር መሰረት ግዥ ለመፈፀም ዘንድሮ 249 ሺህ ብር በጀት መያዙን ተናግረዋል ። እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ እስከ ጥር 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ በዋና ዋና አካባቢዎች የተቋረጡ የመንገድ ዳር መብራት አገልግሎቶች  እንዲጀምሩ ይደረጋል ። በሰቆጣ ከተማ ከ36 ሺህ በላይ ህዝብ ይኖራል ተብሎ እንደሚገመት ታውቋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም