ባሕርዳር ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ልትተገብር ነው

105
አዲስ አበባ ህዳር 3/2011 የባሕርዳርን ከተማ ውበትና ጽዳቷ የሚያረጋግጥ  ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ለመተግበር መዘጋጀቷን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ። ከተማዋን በዙሪዋ ካሉ ከተሞች ጋር የሚያስተሳስር አዲስ መዋቅራዊ ፕላንም በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ እየተዘጋጀ መሆኑን አስተዳደሩ ገልጿል። የከተማዋ ዋና ስራ አስከያጅ አቶ መላክ ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ባሕርዳር በጽዳትና ውበቷ የተሻለች ዓለም አቀፍ ከተማ ብትሆንም የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቷ ግን ዘመናዊ አይደለም። ከተማዋ ውብቷን ጠብቃ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ እንድትቀጥል የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራን ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ያለው አወጋገድ ቆሻሻን ከከተማ ውጭ ባለ ክፍት ማስወገጃ ስፍራ ማጠራቀም እንጂ የቆሻሻን አይነት ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የማያስችል፣ አወጋግድ የአካባቢ ብክለት የሚያስከትል መሆኑን አንስተዋል። ከሚሰበሰበው ቆሻሻ 70 በመቶው ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት የሚያገለግል ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ቆሻሻን ሜዳ ላይ ከማጠራቀም ይልቅ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል አወጋገድ ስርዓት ለመተግበር መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል። በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ለመተግበር ዲዛይን ማሰራቱን ገልጸው፤ የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናት በማድረግ በዚህ ዓመት መጨረሻ ስራ ይጀምራል ብለዋል። ከሚሰበሰበው ቆሻሻ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማምረትም አንድ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንና የማምረቻ መጋዘኑ ስራም 40 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል። በሌላ በኩል የባህርዳር ውበት የሆነው ጣና ሐይቅ ዳርቻ ያሉ ሆቴሎች ሐይቁን የሚበክል ፈሳሽ ቆሻሻ እየለቀቁ መሆኑንም ጠቁመዋል። 'ጣና ሐይቅን የመጠበቅ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው" ያሉት ስራ አስከያጁ፤ በቅርቡ ይህን ድርጊት የፈጸሙ ሆቴሎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል። አያይዘውም  ባህርዳር በዙሪያዋ ካሉ ከተሞችና የገጠር መንደሮች ጋር ተሳስራ እንድትለማ የሚያደርግ መዋቅራዊ ፕላን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። መዋቅራዊ ፕላን የሚዘጋጀው ለ10 ዓመት ነው ያሉት አቶ መላክ፤ የባህርዳር መዋቅራዊ ፕላን ከተማዋ ከ30 ዓመት በኋላ የሚኖራትን ደረጃ በሚያሳይ መልኩ እንደሚዘጋጅ ነው የገለጹት። ለዚህም ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 95 ሚሊዮን ብር በጀት ይዞ እየሰራ ነው ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም