የጃፓን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

114
አዲስ አበባ ህዳር 3/2011 የጃፓን መንግስት የአገሪቱ ባለኃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ግፊት እንዲያደርግ ተጠየቀ። ጥያቄውን ያቀረቡት በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ ናቸው። ዶክተር አርከበ ከጃፓን የውጭ ጉዳዮች የፓርላማ ምክትል ሚኒስትር፣ የኢኮኖሚ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ  ሚኒስትር ዴኤታ፣ ከአገሪቱ  ዓለምአቀፍ ትብብር ኤጀንሲ እና የውጭ ንግድ ድርጅት ምክትል ፕሬዝደንቶችና የፓርላማ አባላት ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። ከተለያዩ ትልልቅ የጃፓን ኩባንያዎች አመራሮች ጋርም ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቅሷል። በውይይቱ ላይ ዶክተር አርከበ የጃፓን ባለኃብቶች ወደኢትዮጵያ ገብተው መዕዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንዲሁም የጃፓንና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እንዲዳብር የሁለቱ አገራት መንግስታት ተግተው መስራት እንዳለባቸውም ገልፀዋል። ከውጭ ጉዳዮች የፓርላማ ምክትል ሚኒስትር እና ከኢኮኖሚ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ውይይት የጃፓን መንግስት ከሀገራችን ጋር ያለውን ትብብር አድንቀው ትብብሩን ለማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች መሰራት አለባቸው ብለዋል፡፡ ልዩ አማካሪው የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዕዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የጃፓን መንግስት ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀው፣ ባለስልጣናቱና የኩባንያዎች ኃላፊዎች በአገራችን ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዲጎበኙ ግብዣ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም ልዩ አማካሪው የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እድሎችን የማስተዋወቂያ የቢዝነስ መድረክ ላይ ከ70 በላይ ለሆኑ የጃፓን ኩባንያዎችና ከተለያዩ ድርጅቶች ለተወጣጡ ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል። ባለሀብቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው መዕዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል። ዶክተር አርከበ እቁባይ፤ ለኢትዮ-ጃፓን ግንኙነት መጠናከር እንዲሁም ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ላበረከቱት አስተዋፅኦ በጃፓን መንግስት ከፍተኛ የሆነውን የሜዳሊያ ሽልማት ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም መሸለማቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያና ጃፓን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1930 ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም