በመዲናዋ ሰብዓዊ ጥሰት ሲካሄድባቸው የነበሩ ስውር እስር ቤቶች ተገኙ

128
አዲስ አበባ ህዳር 3/2011 በአዲስ አበባ ሰብዓዊ ጥሰት ሲካሄድባቸው የነበሩ ሰባት ስውር እስር ቤቶች መገኘታቸውን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ይህን ያስታወቀው ዛሬ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት፣ የሽብርና የሙስና ወንጀሎችን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ላይ ነው። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸምባቸው ቆይቷል። ሰብዓዊ ጥሰቱ የሚፈጸመው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የስውር እስር ቤቶች ውስጥ መሆኑን ያስታወቁት አቃቤ ህጉ፤ በአዲስ አበባ ብቻ 7 እስር ቤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል። ድርጊቱ የተፈጸመው በዋናነት በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አመራሮችና አባላት መሆኑንም አውስተዋል። "ዜጎችን ከአውሬ ጋር ማሰር፣ ብልታቸው ላይ የውሃ ኮዳ ማንጠልጠል፤ እርቃናቸውን ጫካ ውስጥ ማሳደር፣ ጥፍር መንቀል፣ ግብረ ሰዶም መፈጸም፣ የብልት ቆዳን በፒንሳ መሳብ የመሳሰሉ አስነዋሪ ሰብዓዊ ጥሰቶች ይፈጸሙ ነበር" ሲሉ አቃቤ ህጉ ዘርዝረዋል። ተጠርጣሪዎችን ከቦታ ቦታ የሚያንቀሳቅሱት ደግሞ የመንግስት አምቡላንሶችን በመጠቀም መሆኑንም ተናግረዋል። በተፈጸመባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘር መተካት ያልቻሉ እና እጅግ አስከፊ ለሆነ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት የተዳረጉ ዜጎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። በዚህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የተጠረጠሩ 36 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይ ተጠርጣሪዎችን በህግ ጥላ ስር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም