ወላይታ ሶዶ ከነማና ደቡብ ፖሊስ አንድ ለአንድ ተለያዩ

122
ሶዶ ህዳር 3/2011 ወላይታ ሶዶ ከነማና ደቡብ ፖሊስ ትናንት በሶዶ ከተማ ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ አንድ ለአንድ ተለያዩ። ሁለቱ የደቡብ ክልል ክለቦች አቻ የተለያዩት የ2011 የውድድር ዘመን ዝግጅት ክፍተታቸውን ለመለየትና ልምድ ለመውሰድ ባደረጉት የጨዋታ ነው። ወላይታ ሶዶ ከነማ በዚህ የውድድር ዓመት የብሄራዊ ሊግ፣ ደቡብ ፖሊስ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪዎች ናቸው። የወላይታ ሶዶ ከነማ ግቡን ያስቆጠረው በሁለተኛው ደቂቃ በሰባት ቁጥሩ ሰለሞን ጌታቸው ነበር። ደቡብ ፖሊስ ደግሞ አቻ የምታደርገውን ግብ ሄኖክ አየለ በ83ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። በጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከል፣ ኳስ በማደራጀትና በማጥቃት እንዲሁም ወደተጋጣሚው የግብ ክልል ፈጥኖ በመድረስና ሙከራዎችን በማድረግ ወላይታ ሶዶ ከነማ የተሻለ ነበር። በአንጻሩ ደቡብ ፖሊስ መከላከልን መሠረት በማድረግ የመሃል ሜዳውን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሞክሯል። በሁለተኛው የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ ደቡብ ፖሊስ አደራጅቶ በመጫወት በመከላከልና የመሃል ሜዳውን በመቆጣጠር የተሻለ የጨዋታ ፍሰት አሳይቷል። ይሁን እንጂ ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስና በርካታ ሙከራዎች በማድረግ ረገድ ወላይታ ሶዶ ከነማ የተሻለ ነበር። ደቡብ ፖሊስ ከ80ኛው ደቂቃ ጀምሮ ለተመልካቾች አዝናኝ በሆነ ጨዋታ የመሃል ሜዳውን ብልጫ ከመውሰድ ባለፈ፤ ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ ባለሜዳውን ሲያስጨንቅ ነበር። በዚህ አጋጣሚ ነው በ21 ቁጥሩ አማካይነት ከመሃል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮና የተጋጣሚው ቡድን የተከላካይ ክፍል አለመረጋጋትን ተጠቅሞ አቻ ያደረገችውን ግብ ያስቆጠረው። የወላይታ ሶዶ ከነማ ዋና አሰልጣኝ ኃብተማሪያም ጳውሎስ ጨዋታው ክፍተታቸውንና ጥንካሬያቸውን ለመለየት እንደረዳቸው ገልጸዋል። ክለቡ ከተቋቋመ ሦስተኛ ዓመቱ ቢሆንም ወደ ብሄራዊ ሊግ ያደገና በወጣቶች የተሞላ መሆኑን ተናግረዋል። ተጋጣሚያቸው በፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወት ጠንካራ ክለብ በመሆኑ ጨዋታው ብዙ ግብ ማስቆጠርና ያስቆጠርነውን አስጠብቆ ከመውጣት አንጻር ክፍተቶቻችንን አሳይቶናል ብለዋል። ''በዝቅተኛ ሊግ ላይ ከሚጫወት ክለብ ጋር ስትገናኝ ሁልጊዜም ከፍተኛ ብልጫ ይኖራል ወይም በከፍተኛ ፍላጎት ስለሚጫወት ውጥረት ውስጥ የመክተት አጋጣሚ አለ'' በማለት የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ፖሊስ ክለብ አሰልጣኝ ዘላለም ሺፈራው ናቸው። ተጋጣሚያቸው ካለው ፍላጎት የተነሳ ጫና ፈጥሮባቸው ቢቆይም፣ ኋላ ላይ መድከሙን ተጠቅመው አቻ መውጣታቸውን ተናግረዋል። የፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ እንደመሆናቸው መጠን ውጤቱና በጨዋታው ያሳዩት ፉክክር እንደማይመጥናቸው ገልጸው፣ በተለይም ግብ ማስቆጠርና የተደራጀ መከላከልን ለመፍጠር እንሰራበታለን ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም