ድሬዳዋን ሕገ-መንግሥታዊ ዕውቅና የሌላው መተዳደሪያዋ በአስቸኳይ ሊነሳላት ይገባል ተባለ

195
ድሬዳዋ ህዳር 2/2011 ድሬዳዋ በሚፈለገው ደረጃ እንዳታድግና በየደረጃው የሚገኘውን ሕዝብ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን እንቅፋት የፈጠረው ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና የሌለው ቻርተር በአስቸኳይ ሊነሳላት እንደሚገባ  የሕግ ባለሙያዎች ተናገሩ። የህግ ባለሙያዎቹና ''ሳተናው'' የተባለ የድሬዳዋ ወጣቶችን ያካተተ ኅብረት ከድሬዳዋ አመራሮች ጋር በማህበራዊና በምጣኔ ሃብታዊ፣ በመልካም አስተዳደርና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ ባለሙያዎቹና ወጣቶቹ በዚሁ ጊዜ ከተማዋ ዕድገቷ ተጠብቆና ነዋሪዎቿም የልማትና የምልካም አስተዳደር ተጠቃሚዎች የሚሆኑበት አስተዳደራዊ መዋቅር ሊፈጥርላት እንደሚገባ አሳስበዋል። የሕግ ባለሙያው አቶ ፉህሚ ዳንኤል ከተማዋ ለፌደራል መንግሥት ተጠሪ የምትሆንበት ሕገ-መንግሥታዊ መሠረትና እውቅና በሌለበትና የሕገ-መንግሥቱን የበላይነት ባላከበረ ቻርተር እንድትመራ መደረጉ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት ሕጋዊ መሠረት በሌለው ቻርተር መመራቷ  በአስተዳደሩና በነዋሪዎቹ ኑሮ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረም ተናግረዋል፡፡ ቻርተሩ በከተማው አስተዳደር ከሚንቀሳቀሱ ግዙፍ ኢንቨስትመንትና ፋብሪካዎች ከፌደራል መንግሥት መካፈል የሚገባትን ገቢ እንዳሳጣትም አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ቻርተሩ በአስተዳደሩ ውስን ሃብት የሚተዳደረውን የፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱን ለፌደራል መንግሥት ማድረጉ ሕግ ተርጓሚው አካል በተዛባ መንገድ እንዲደራጅ፣ ያለአግባብ ሥልጣን መስጠቱ ደግሞ የሕግ የበላይነት እንዳይሰፍንና በተቀናጀ መልኩ እንዳይሰራ ክፍተት መፍጠሩን ባለሙያው አብራርተዋል፡፡ ሌላው የሕግ ባለሙያ አቶ ይትባረክ አስፋው በበኩላቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለከተማዋ  ሕግ የማውጣት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ እንዳልተሰጠው ይገልጻሉ። ይህ የሕግ መሠረት በሌለበት ከተማዋ  በቻርተር እንድትመራ መደረጉ ለማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት ዳርጓታል ብለዋል፡፡ ቻርተሩ የድሬዳዋን 99 በመቶ መልክዓ ምድርና ገሚስ ነዋሪዎቿን የማያውቅ በመሆኑ ከፌደራል መንግስት የሚመደበው የበጀት ድጎማ ዝቅ እንዲልም አድርጓል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ቻርተሩ ድሬዳዋን በአንድ በኩል በውስጧ ያለውን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሃብት ከሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ማግኘት የሚገባትን ገቢ እያሳጣ በሌላ በኩል የድጎማ በጀቱን ስለሚያስነስባት ሕዝቧ በየደረጃው የሚያነሳውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ መቸገሯንም አቶ ይትባረክ አመልክተዋል፡፡ የአስተዳደሩን ካቢኔ በቀላሉ የማፍረስ አቅም ያለው ቻርተር በአስቸኳይ መፍትሄ መስጠትና ለሕዝቡን ጥያቄዎች መመለስ  ይገባል ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ባለሙያዎቹ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች መሠረታዊና አስተዳደሩና ሕዝብ ከሚፈልጉት የውጤት ላይ እንዳይደርስ ያደረጉ መሠረታዊ ክፍተቶች መሆናቸውን አምነዋል፡፡ በቻርተሩ ላይ የተቀመጡ ክፍተቶችን በመንቀስ አስቸኳይና ፈጣን መፍትሄ እንዲሰጠው ለሚመለከታቸው የፌደራል መንግሥት ተቋማት ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ''ድሬዳዋን አላራምድ ያሉ የህግ ክፍተቶች  እንዲታረሙ የተሰጡ አስተያየቶችን በማከል ወደሚመለከተው የፌደራል መንግስት ይላካሉ። የገቢ ክፍፍል ክፍተትን ለማረም የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል''ብለዋል ከንቲባው፡፡ አስተዳደሩ  በ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት እያደገ  የመጣውን  የሕዝቡን ልማት ጥያቄዎች በፍጥነት ለመፍታት እንደማያስችለው  የገለጹት አቶ ኢብራሂም፣ክፍተቱን ለመሙላት የሚያስችል ሥራ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ወጣት ምሁራን በብሔርና በኃይማኖት ሳይለያዩ የአስተዳደሩን ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ድርሻቸውን እንዲያሳድጉም ከንቲባው  ጠይቀዋል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ካቢኔ አባል አቶ አወል አብዲ የከተማዋን ዕድገት የገታውና ያልተማከለ አስተዳደር ባለቤት ያደረጓትን ሕጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነገጋር መፍትሄ ይፈለግላቸዋል ብለዋል፡፡ ቻርተሩ የሕዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ችግር በመፍጠር መሪዎቿን ወደፊት አላራምድ ብሏቸዋል ያሉት አቶ አወል፣ይህም በገቢ፣ በፍትህ፣በፀጥታ ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ መፍትሄ ለመስጠት እንዳላስቻላቸው ገልጸዋል፡፡ የአስተዳደሩን ችግሮች ለመፍታት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)በጥምረት ከሚያስተዳድረው ከሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ሶሕዴፓ) ጋር  እንደሚሰራ አረጋግጠዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም