የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፋይናንስ አገልግሎት በተጨማሪ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነ አመለከተ

58
አዲስ አበባ ህዳር 2/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚሰጠው የፋይናንስ አገልግሎት በተጨማሪ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና ገለጹ። ባንኩ ለዋና መስሪያ ቤት የሚያስገነባውን የባለ 48 ፎቆ ህንፃ ግንባታ የመጨረሻ ፎቅ የአርማታ ሙሌት ስራ ግንባታውን ከሚያከናውነው ከቻይናው ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪግ ኩባንያ ጋር በመሆን በልዩ ዝግጅት አከናውኗል። በዚሁ ወቅት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና እንደገለጹት፤ ባንኩ በአዲስ አበባ እያስገነባ ያለው በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ህንጻ ከፋይናንስ አገልግሎት በተጨማሪ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ እንዲገኝ አድርጎታል። የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲመጣ፣ በግንባታው ፕሮጀክት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በማካተት በአማካሪነትና በተቆጣጣሪነት እውቀትና ክህሎት አገር ውስጥ እንዲቀር የማድረግ ሥራ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። በኮንስትራክሽን ሙያ የተሰማሩ ባለሙዎች፣ አሰሪዎችና ሰራተኞች የህንፃውን የግንባታ ቴክኖሎጂ እንዲጎበኙና እንዲያስፋፉ የማድረግ ሥራም እየተሰራ ነው ብለዋል። ባንኩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በየጊዜው ስፖንሰር በማድረግ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ውጭ አገር ሄደው የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲቀስሙ እያደረገ እንደሆነ አክለዋል። የህንፃው ግንባታ ሲጠናቀቅ በተለያዩ ቦታ የሚገኙ የዋና መስሪያ ቤቱ ቢሮዎች በአንድ ቦታ ተሰብስበው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ ከ2ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ስብሰባ ማዘጋጀት የማስቻል፣ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል እንዲኖር ያስችላል። ከህንፃው የመጨረሻ 48 ወለል ላይ ሆነው ማንም ሰው የአዲስ አበባን እይታ እንዲጎበኝና በምስራቅ አፍሪካ በትልቅነቱ ዋነኛ በመሆን ለውበት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተሰራ ነው። ይህም ህንፃው ሲጠናቀቅ አገሪቷ በ2025 በባንክ አገልግሎት መስክ ልትደርስበት ያስቀመጠችውን ራእይ ያሳካል ብለዋል። ግንባታውን እያካሄደ የሚገኘው ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዛዎ ሹን እንደተናገሩት፤ የህንፃው ግንባታ ፕሮጀክት በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያሉ ሰራተኞች ግንኙነታቸውንና ወዳጅነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያደረገና የራሱን ምስክርነት የሰጠ ነው። ከአገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች በተለይም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተውጣጡ ከ90 በላይ ቡድኖች ነፃ የስራ ላይ ልምምድ እንዲያገኙ ያስቻለ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። ከአንድ ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር የቻለ ሲሆን በበጎ ተግባር ስራ ላይ ለተሰማሩ 12 ድርጅቶችም ትብብር በማድረግ የራሱን አስተዋፆኦ ማበርከት የቻለ ፕሮጀክት እንደሆነ ጠቁመዋል። ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ከ 5ሺህ በላይ ጎብኚዎች የጎብኙት ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል። በስራቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች ቻይና ሄደው ነፃ የትምህርት እድል እንዲያገኙና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ መደረጉንም አክለዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታው እየተጠናቀቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያና የቻይና ሰራተኞች የባህል ልውውጥና የእርስ በእርስ መስተጋብራቸው እንዲዳብር ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አቶ ኢሳያስ ገብረዮሐንስ የግንባታው ፕሮጀክት ክፍተት ባለብን ቦታዎች ላይ ከ45 በላይ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ አስችላል። ፕሮጀክቱ በተለያዩ የዲዛይን ስራዎች ላይ ከ13 በላይ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ አድርጓል። ይህም የግንባታው ፕሮጀክት በአጠቃላይ በአገርና በተለይም በኢንስቲዩቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፈ ብዙና መጠነ ሰፊ የሆነ ጥቅም በማስገኘት አርአያ ሆኖ የሚጠቀስ ነው ብለዋል። ለህንፃው ግንባታ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግ  ሲሆን ግንባታው እ.አ.አ በ2020 ያልቃል ተብሎ ይጠበቃል። ህንፃው 193.85 ሜትር ከፍታ ሲኖረው በምስራቅ አፍሪካ በከፍታው ግንባር ቀደምት ይሆናል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም