በምስራቅ ጎጃም 70 ሺህ ሄክታር መሬት ዳግመኛ እየለማ ነው

48
ደብረማርቆስ ህዳር 1/2011 በምስራቅ ጎጃም 70 ሺህ ሄክታር መሬት በዳግም ልማት በተለያየ  የሰብል ዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። ልማቱ እየተካሄደ ያለው አርሶአደሩ በመኽር የዘራውን ሰብል በመሰብሰብ በቀሪ እርጥበትና አሁን እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቀሪ እርጥበት ዳግም እንዲለማ ከታቀደው ውስጥ እንደሆነ በመምሪያው  የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ እያለ ዳኘ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ እቅዱን ለማሳከትም አሁን እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም አርሶ አደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየተቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እየጣለ ያለው ዝናብ በተወሰነ ደረጃ በደረሰ ሰብል  ላይ ተጽዕኖ ቢኖረውም በቀሪ እርጥበት ለተዘሩና ለመዘራት ለተዘጋጁ  ጠቃሜታ እንዳለው አብራርተዋል። እየለማ ካለው ሰብል ውስጥ ጓያ፣ ሽንብራ፣ ምስር፣ ገብስ፣ ጤፍና ስንዴ ይግኝበታል፡፡ በቀሪ እርጥበት ልማቱ 105 ሺህ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ከ2 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡ በደጀን ወረዳ የጢቅ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተገኘ በቃሉ በሰጠት አስተያየት አሁን እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም በመኸር ወቅቱ ያለሙትን ሰብል በመሰብሰብ ሁለተኛ ዙር ልማት እያካሄዱ እንደሚገኙ  ገልፀዋል። አርሶ አደሩ እንዳሉት መስከረም ላይ  በቀሪ እርጥበት ሩብ ሄክታር ማሳ ጓያ ዘርተዋል፤ ሰሞኑን እየጣለ ባለው ዝናብ ደግሞ ከግማሽ ሄክታር በላይ ገብስ ለመዝራት የእርሻ ስራ እያከናወኑ ነው። በዚህም ከ30 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ የገለጹት አርሶ አደሩ ባለፈው ዓመት በቀሪ እርጥበት ካለሙት ግማሽ ሄክታር ማሳ ከ12 ኩንታል በላይ የአብሽ ምርት እንዳገኙ  አስታውሰዋል። በአነደድ ወረዳ የወጀል ቀበሌ አርሶአደር ልጃአለም ጸጋሁን በበኩላቸው ባለፈው መስከረም ወር ላይ ግማሽ ሄክታር ጓያ የዘሩ መዝራታቸውን አመልክተው ከጥቅምት ወር አንስቶ እየጣላ ባለው ዝናብ  ከግማሽ ሄክታር በላይ ድንች መዝራታቸውን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በሩብ ሄክታር ማሳ ጓያ በመዘራት 15 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አስታውሰው ዘንድሮ ደግሞ እስከ 80 ኩንታል የድንች ምርት እንደሚጠብቁ አስረድተዋል። ባለፈው ዓመት 50 ሺህ ሄክታር ማሳን በቀሪ እርጥበት ዳግም በማልማት ከ1 ሚሊዮን 300ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም