የሸማቾች ትስስር ካርድ ስርጭቱ ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ መከለስ ይገባዋል-ሸማቾች

90
አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 በአዲስ አበባ ከተማ በሸማቾች ካርድ ስርጭት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሸማቾች የሕብረት ስራ ማህበራት ለሕዝቡ የሚሰራጩ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተለይም ስኳር፣ዘይትና ዱቄትን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ የትስስር ካርድ 'ኩፖን' ስራ ላይ ውሏል። ይህ አሰራር መሰረታዊ ፍጆታዎችን ለሸማቾች ተደራሽ  በማድረጉ ረገድ ለውጥ ቢያስገኝም አንዳንድ ነዋሪዎች  ከአንድ በላይ መጠቀሚያ ኩፖን ወስደው ግዥ ሲያካሒዱ ይስተዋላል። በሌላ በኩል ቀደም ሲል ኩፖኑን ለመስጠት በየወረዳው ምዝገባ በተደረገበት ወቅት እድሉን ያላገኙ ነዋሪዎች ከሸማቾቹ የቁሳቁስ ግብይት ለማድረግ ይቸገራሉ። አስተያያታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ሸማቾች እንደተናገሩት የፍጆታ እቃዎችን በፍትሐዊነት ለማዳረስ የትስስር ካርድ ተደራሽነት ማሻሻልና እንደ አዲስ መፈተሽ አስፈላጊ ነው። በልደታ ክፍለ ከተማ የወረዳ 3 የልደታ ፋና ማህበር ሂሳብ ሹም አቶ ወንድማገኝ ሞገስ እንዳሉት ቀደም ሲል የነበረ አሰራር  ለህብረተሰቡ ሸቀጦችን ለማከፋፈል የተሰጠው  ኮታ የተጠና ባለመሆኑ ፣ በመልሶ ማልማት የሚሄዱ ሰዎች ና ተመልሰው የሚገቡ ሰዎችን ታሳቢ ባለማድረጉ  በአዲስ መልክ መጠናት አለበት ይላሉ፡፡ የልደታ ነዋሪ አቶ እሸቱ ብርሃኑ በበኩላቸው  አዳዲስ ሰዎችንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአዲስ የኩፖን ስርጭት የሚሰራጭበት አግባብ መፈጠር አለበት ይላሉ፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ በሕብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ የፋይናንስና የገበያ ትስስር ኦፊሰር አቶ ዮሴፍ ወርቅነህ  በበኩላቸው ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በሚለቁበት ወቅት በአቅራቢያቸው ብቻ እንዲጠቀሙ የሚደረግ ቢሆንም ከአንድ ቦታ በላይ ተጠቃሚ የሚሆኑ እንዳሉም ነው የሚናገሩት። በመሆኑም  ይህን መሰል ችግር ለማስወገድ በቀጣይ በአዲስ መልክ ምዝገባውን የማጣራት ስራዎች እንደሚሰሩ ነው ያብራሩት። በጉለሌ ክፍለ ከተማ  ወረዳ 5 በብርሃን ሸማቾች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይታገሱ ጠናም ሸማቾች ከአንድ በላይ የትስስር ካርድ ይዘው ያለአግባብ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ከንግድና ኢንደስትሪ ጋር በቅንጅት ስለምንሰራ ችግር አላጋጠመንም ይላሉ። በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ሬጉላቶሪ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን በየነ በትስስሩ ካርድ ስርጭት ላይ ያለውን ክፍተት በመጠቀም አለ አግባብ ተጠቃሚ የሚሆኑ ግለሰቦች መኖራቸውን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ከመጀመሪያው ልምድ በመውሰድና የተጠናከረ መረጃ በማሰባሰብ በአዲስ መልኩ የትስስር ካርድ ስርጭት ለማካሄድ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተሰበሰበው መረጃ መሰረት ከ1 ሚሊዮን 77 ሺህ በላይ የትስስር ካርዶች በአዲስ መልክ እንደሚታተሙም አክለዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም