በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተገኙ ግለሰቦች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተገኙ ግለሰቦች ተያዙ
59
መተማ ግንቦት 15/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ በኩል በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተገኙ አምስት ግለሰቦች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በፌደራል ፖሊስ የሰሜን ዲቪዥን ሁለተኛ ሻለቃ አዛዥ ኮማንደር ደግነው በለንጎ እንደገለፁት ግለሰቦቹ የተያዙት ፖሊስ ባደረገው ክትትል ትናንት ማምሻውን ነው ። በህገ ወጥ ደላሎች ተታለው ከሃገር ሊወጡ ሲሞክሩ የተያዙት ግለሰቦቹ ከድሬዳዋ የመጡ እንደሆኑ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። ኮማንደሩ እንዳሉት ግለሰቦቹ ከዞኑ ዋና ከተማ ገንዳውኃ ወደ መተማ ዮሃንስ በባጃጅ ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ እንዳሉ በድንገተኛ የበረራ ፍተሻ ተደርሶባቸው መያዝ ተችሏል፡፡ ህገ ወጥ አዘዋዋሪ ደላላ ነው የተባለ ግለሰብም መያዙን ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች ቀሪ አራት ወንድና አንድ ሴት ተዘዋዋሪዎች ደግሞ በጫካ ውስጥ እንዳሉ መረጃ እንደደረሳቸውና እነሱን ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ከተያዙት ግለሰቦች መካከል ወጣት ሙሃመድ አብዱልከሪም እንደተናገረው ከድሬዳዋ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ለደላላ እያንዳንዳቸው 11 ሺህ ብር ከፍለዋል። በስምምነታቸው መሰረትም በሱዳን በኩል ወደ ሊቢያ ከዚያም ወደ ጀርመን ለማሸጋገር እንደሆነና በመጨረሻም 180 ሺህ ብር ድረስ ለመክፈል እንደሆነም ገልጿል። ሆኖም ከድሬደዋ ተነስተው ከሁለት ቀናት ጉዞ በኋላ መተማ መድረሳቸውን የተናገረው ወጣቱ በአካባቢው ባለ ጫካ ውስጥ ቆይተው ዋናውን ጉዞ ሳይጀመሩ በፖሊስ መያዛቸውን አስረድቷል፡፡ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት በቅርቡ በአካባቢው በተቋቋመው ጥምረት ለኢትዮጵያ የስደተኞች ማረፊያና መረጃ ማዕከል የመኝታ፣ የምግብና ሌላም አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን የማዕከሉ አስተባባሪ ይሄነው ሞላ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንደሚያደርሷቸውም ጠቁመዋል፡፡