የእስራኤል ኘሬዚዳንት ሬዩቪን ሪቭሊን አዲስ አበባ ገቡ

72
አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2010 የእስራኤል ኘሬዝዳንት ሬዩቪን ሪቭሊን ለሶስ ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ። ኘሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያምና አምባሳደር ሱሌማን ደደፎን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ለሦስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ኘሬዚዳንት ሬዩቪን ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ከመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል። በኘሬዚዳንት ሪቭሊን የሚመራው የእስራኤል የልዑካን ቡድን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ያቀፈ እንደሆነ ተገልጿል። ሬዩቪን ሪቭሊን ኢትዮጵያን የሚጎበኙ የመጀመሪያው የእስራኤል ኘሬዚዳንት ናቸው። የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ግንኙነት ከጀመረ ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ኢትዮጵያና እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1956 ነው። ሁለቱም አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ኤምባሲ ከፍተው እየሰሩም ይገኛሉ። ሁለቱ አገሮች በግብርና ዘርፍ ጠንካራ ትስስር ያላቸው ሲሆን በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በደህንነት፣ በጸጥታና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ላይም ጠንካራ የጋራ ትብብር አላቸው። የኢትዮጵያና እስራኤል የንግድ ልውውጥ 60 ሚሊዮን ዶላር እንደደረሰ መረጃዎች ያመለክታሉ። የእስራኤሉ ኩባንያ 'ጊጋዋት ግሎባል' የስራ ሃላፊዎች በያዝነው ዓመት ታህሳስ ወር መጨረሻ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በነበራቸው ውይይት በኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይልና በሰው ሀብት ልማት የ500 ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ እንደሚያፈስ ገልጾ ነበር። ኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ቡና፣ ቅመማ ቅመሞች፣ የቅባት እህሎች፣ የፍራፍሬና የጥራጥሬ ምርቶችን ስትልክ፤ የካፒታል እቃዎች፣ ማሽነሪዎች፣ የፕላስቲክ፣ የብረታ ብረትና የኬሚካል ውጤቶችንና የምግብ ምርቶችን ታስገባለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም