በካፋ ዞን የተከሰተውን አለመረጋጋት ወደ ነበረበት የመመለስ ስራ እየተከናወነ ነው...አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ

58
ሀዋሳ ህዳር 1/2011 በካፋ ዞን ስለ ቡና መገኛነት በድረ-ገጽ በተላለፈ መረጃ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ወደ ነበረበት ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ገለጹ። ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በካፋ ዞን የተፈጠረው አለመረጋጋት ከቡና መገኛነት ጋር በተያያዘ በድረ-ገጾች በተላለፈ መረጃ አማካኝነት ነው። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፍረንስ በቅርቡ ለማዘጋጀት በሚያደርገው ሂደት በድረ-ገጹ የተላለፈው መረጃ የካፋን ወጣቶችና ህዝቡን አስቆጥቶ በአካባቢው አለመረጋጋት ተፈጥሯል። “የቡና ባለቤትነት ጥያቄን በሚመለከትም የባለቤትን ጉዳይን የሚመራና እውቅና የሚሰጥ ራሱን የቻለ ተቋም በሃገር ደረጃ ያለ በመሆኑ ጥያቄው አሰራሩን ተከትሎ ምላሽ ያገኛል”ብለዋል፡፡ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ያቀረበው የካፋ ህዝብና ወጣት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሲገታ የሚያሳድረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በመረዳት የተዘጉ መንገዶችን እንዲከፍት ጠይቀዋል፡፡ በአካባቢው ያሉ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ይህንን በማስተባበርና ወጣቱም ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመልስ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችም አሁን ላይ ወደ ሰላም እየተመለሱ መሆናቸውን ገልጸው የአብዛኛዎቹ መንስኤም ከመዋቅር ጋር የተያያዙ እንደነበሩ ጠቁመዋል። በቅርቡ የክልሉ ምክር ቤት 44 ወረዳዎችንና 3 ዞኖችን በአዲስ መልክ ማዋቀሩን ተከትሎ አዳዲስ ፍላጎቶች የፈጠሩት ስሜትና የሚጠበቅ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ “ችግሮቹን በቀጣይ ከህዝቡ ጋር በሚደረግ ጥልቅ ውይይት መስመር የሚይዙ ናቸው” በማለት  በየደረጃው ያለ አመራር ከህዝቡ ጋር በሚያደርጋቸው ሰፊ የውይይት መድረኮች እንደሚኖሩ ገልጸው በዚህም የሰላም ግንባታ ስራው እንደሚጠናከር ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም