ባምላክ ተሰማ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ባሳየው ብቃት አድናቆት ተችሮታል

75
አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ትናንት ማምሻውን በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ባሳየው ብቃት አድናቆትን አግኝቷል። በቱኒዚያው ኤስፔራንስ ዴ ቱኒዝ በግብጹ አል-አህሊ መካከል የተደረገውን ጨዋታ በብቃት መምራቱን ተከትሎ ነው አድናቆት እየተቸረው ያለው። በቱኒዚያ በተካሄደው ሁለተኛ ዙር የ2018 ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ኤስፔራንስ ዴ ቱኒዝ የግብፁ አል-አህሊን 3 ለ 0 በመርታት በድምር ውጤት 4 ለ 3 አሸንፏል። በኦሎምፒክ ደ ራዴስ ስታዲየም የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት አህመድ አሀመድ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ተከታትለዋል። ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ሁለቱን ቡድኖች በመምራት ወደ ሜዳ ይዘው የገቡ ሲሆን ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር የታየበት እንደነበር የአፍሪካና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። በጨዋታው ሂደት ባምላክ ከጨዋታው ክብደት አንፃር ተገቢ ውሳኔዎችን በመወሰን፣ በአግባቡ ጨዋታውን በመቆጣጠርና የጨዋታውን ሚዛን በመጠበቅ ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱ ተገልጿል። የጨዋታውን መጠናቀቅ ተከትሎም ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ከፊፋ ፕሬዝዳንት ሜዳሊያ ተረክቧል። ፈረንሳዊው የአል-አህሊ አሰልጣኝ ፓትሪስ ካርቴሮን ከጨዋታው በፊት ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ጠንካራና ውጥረት የተሞላበትን ጨዋታ በብቃት እንደሚመራና እንደሚቆጣጠር ያላቸውን እምነት ገልጸው የነበረ ሲሆን ባምላክ በጨዋታው ላይ ይሄንኑ በተግባር አሳይቷል። ዳኛው በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት በ2017 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የግብጹ አል-አሀሊና የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ ያደረጉትን የመጀመሪያ ዙር የፍጻሜ ጨዋታ መምራቱም የሚታወስ ነው። ከሰኔ 4 እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ.ም በሩሲያ በተካሄደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ የ37 ዓመቱ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ኢትዮጵያን በመወከል በአራተኛ ዳኝነት የምድብ ጨዋታዎችን መምራቱም አይዘነጋም። በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የአገራትና የክለብ ውድድሮች ላይ ጨዋታዎችን በመምራት የረዥም ጊዜ ልምድ ያለው ባምላክ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2009 የፊፋ የዳኞች ዝርዝር ውስጥ በመግባት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ጨዋታዎችን በመሐል ዳኝነት በመምራት ላይ ይገኛል። የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ዴ ቱኒዝ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግን ለሶስተኛ ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን የዘንድሮ አሸናፊነቱን ተከትሎ የ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደሚያገኝ ተገልጿል። በተጨማሪም ክለቡ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊነቱ በታህሳስ 2011 ዓ.ም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው የፊፋ የዓለም የክለቦች ዋንጫ ውድድር ላይ አፍሪካን ወክሎ ይሳተፋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም