የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ህዳር 9 ይጀመራል

84
አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 የ2011 ዓ.ም የሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን ፕሪሚየር ሊግ ህዳር 9 ቀን ይጀመራል። 12 ቡድኖች የሚሳተፉበት የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ-ግብር በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳል። በዚሁ መሰረት ህዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከመከላከያ፤ በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከጥሩነሽ ዲባባ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በክልል ከተማ በዲላ ስታዲየም ጌዲኦ ዲላ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይጫወታሉ። ህዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም አዲስ አበባ ከተማ ከጥረት ኮርፖሬሽን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት፤ ኢትዮ-ኤሌትሪክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 11 ሰዓት ይገናኛሉ። ህዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል። የቀጣይ ሳምንት መርሃ-ግብሮችን በቀጣይ ጊዜያት ይፋ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በተመሳሳይ 10 ክለቦች የሚሳተፉበት የ2011 ዓ.ም የሴቶች ሁለተኛ ዲቪዚዮን ፕሪሚየር ሊግ ህዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጀመርም ለማወቅ ተችሏል። ደደቢት የ2010 ዓ.ም የሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን እንደነበር ይታወሳል። በሴቶች እግር ኳስ ጠንካራ እና ውጤታማ ቡድን የነበረው ደደቢት የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ክለቡ አጋጠመኝ ባለው የገንዘብ ችግር ምክንያት በዘንድሮ ዓመት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ እንደማይሳተፍ መግለጹ ይታወቃል። ክለቡ ላለፉት ሶስት ዓመታት የሊጉ ውድድር አሸናፊ በመሆን በሴቶች እግር ኳስ የበላይነቱን የያዘ ሲሆን የቦታ ለውጥ (ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ) ማድረጉን ተከትሎ እና በገንዘብ እጥረት የወንድ እና የሴት ቡድኑን ይዞ መጓዝ ስለሚቸገር የሴቶች ቡድን ዘንድሮ እንዳያማያሳትፍ ማሳወቁም ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም