የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱ አገር አቀፍ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ሊፈጥሩ መሆኑን ገለጹ

101
አዲስ አበባ ህዳር 1/2011  በኢትዮጵያ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የሚያራምዱ ፓርቲዎች ጥምረት ሊመሰርቱ መሆኑን አገር አቀፍ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። በኢትዮጵያ በዜጎች መካከል ያለውን አንድነት ለማጎልበት በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የተሻለ አማራጭ መሆኑንም ፓርቲዎቹ ጠቁመዋል። አገር አቀፍ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ካሁን በፊት እንደነበረው ውህደት ከፈጠሩ በኋላ መልሰው የሚበታተኑበት አጋጣሚ እንዳይከሰትም በርዕዮተ ዓለምና በአስተሳሰብ ተመሳሳይ ከሆኑ ፓርቲዎች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ጋር ቅድመ ውይይት እያደረጉ መሆኑንም አስታውቀዋል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት "የዜግነት ፖለቲካ ከሚያራምዱ አካላት ጋር ጥምረት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ጀምረናል" ብለዋል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ፕሬዘዳንት ዶክተር በዛብህ ደምሴ እንደሚሉት ድርጅታቸው "ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላምና እድገት የሚበጃት የዜግነት ፖለቲካ" መሆኑን በመገንዘብ ከ26 ዓመታት በላይ ሲታገል ቆይቷል። በቀጣይም በኢትዮጵያ የወጣቶች እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ ሰላም እንዲሰፍን፣ አንድነት እንዲጎለብትና ጠንካራና ተወዳዳሪ ለመሆን  ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት እየተወያየን ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ "የዜግነት እንጂ የብሄር ፖለቲካ እንደማያዋጣት አይተናል" የሚሉት ዶክተር በዛብህ፤ በጥምረቱ ከውጭ ሲታገሉ የነበሩ የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱ ድርጅቶችም እንደተካተቱ ፍንጭ ሰጥተዋል። በቀጣይ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ከተከተለ በምርጫ 1997 ዓ. ም መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ቀስተ ደመና እና አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲን በማዋሃድ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲን በመፍጠር አዲስ አበባ ከነበሯት 138 መቀመጫዎች 137ቱን ያሸነፍንበትን ድል ወደፊትም በጥምረት እንደግመዋለን ብለዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ በበኩላቸው ፓርቲያቸው ጠንካራና ተወዳዳሪ ለመሆን በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ተቀራራቢ ከሆኑ ፓርቲዎች፣ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ጋር  ውህደት ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ "ዴሞክራሲን ለማጎልበት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥራቸውን ከማብዛት ተቀናጅተው ጠንካራና ተወዳዳሪ መሆን አለባቸው" ያሉትን ከቃል ባለፈ በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋልም ብለዋል። ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ፓርቲዎች ጥምረት በፈጠሩ በማግስቱ እንዲለያዩ የሚያደርጋቸው "ከውጭ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ከውስጥ ደግሞ የፓርቲ አመራሮች ድክመት" እንደነበር ገልጸዋል። ከዚህ በፊት በውጫዊ ተፅዕኖ ምክንያት ይደርስ የነበረው የመበተን አደጋ ወደፊት እንደማይከሰት ተስፋ አድርጋለሁ ያሉት አቶ የሽዋስ "ውስጣዊ ችግሮቻችንንም በሰከነ መንፈስ ተወያይተን እናስወግዳቸዋለን" ብለዋል። "የአንድነትና መኢአድን ውህደት ያፈረሱት 'ደህንነት ነን' የሚሉ አካላት" እንደሆኑም ገልጸው፤ ከዚህ በኋላ ግን ውጫዊ ተፅዕኖ ሊኖር እንደማይችል በመንግስት ላይ እምነት መጣላቸውንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም