አፍሪካዊያን የጣና ሃይቅን ሊንከባከቡት ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

60
ባህርዳር ህዳር 1/2011 ሁሉም አፍሪካዊ የጣና ሃይቅን ከቪክቶሪያ ሃይቅ በመቀጠል ሊንከባከበው ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከኤርትራና ሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች ኢሳይያስ አፈወርቂ እና መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ጋር መርቀው በከፈቱት የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝ ሆስፒታል የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ ነው። የሶስቱ አገራት መሪዎች ከሆስፒታሉ ምርቃት በፊት የጣና ሀይቅን በጀልባ የጎበኙ ሲሆን ጥንታዊ ገዳማትንም አይተዋል። ዶክተር አብይ እንደገለጹት ታንዛንያ፣ ኡጋንዳና ኬንያን ከሚያካልለው የቪክቶሪያ ሃይቅ በመቀጠል የጣና ሃይቅን ሁሉም አፍሪካዊ ሊንከባከባው ይገባል። የጣና ሃይቅ ያለው ሰፊ ሃብት ለኢትዮጵያና ጎረቤት አገራት ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያንም የሚተርፍ በመሆኑ ሁሉም አፍሪካዊ ሊንከባከበው፣ ኩራት ሊሰማውና ሊያከብረው ይገባል ብለዋል። 3 ሺህ 600 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የጣና ሃይቅ ያለው ታሪክና ሃብት ሰፊ በመሆኑ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ሊኮሩ ይገባልም ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶማሊያና ከኤርትራ ፕሬዝዳንቶች ጋር በክልሉ ያደረጉት ቆይታ ታሪካዊ እንደነበርም ነው የተናገሩት።                                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም