የጥበበ ጊዮን ሆስፒታል ስራ ፍሬያማ እንዲሆን መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል - ዶክተር አብይ አህመድ

76
አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ ፍሬያማ እንዲሆን መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂና ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ዛሬ በባህርዳር ዩንቨርስቲ የተገነባውን ሆስፒታል መርቀው ከፍተዋል። ዶክተር አብይ የዩንቨርስቲውና የሆስፒታሉ ሃላፊዎች የህክምና መሳሪዎች እንዲሟሉ ላቀረቡት ጥያቄ መንግስትና የአማራ ክልል በጋራ በመሆን ለጥያቄው ምላሽ እንደሚሰጡም አረጋግጠዋል። መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በሆስፒታሉ አቅም የሚሰሩ ስራዎችን የሆስፒታሉ የስራ ሃላፊዎች ማከናወን እንደሚገባቸውና አረንጓዴና ጽዱ ከተማ የሆነችውን የባህርዳር ከተማ ገጽታ የሚያሳይ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። ለሆስፒታሉ ግንባታና አጠቃላይ ስራ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ዛሬ ከባህርዳር ዩንቨርስቲ የተመረቁ የህክምና ዶክተሮች በሙያቸው ተግተው በመስራትና ለህክምናው ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ተመራቂ ተማሪዎቹ በሶማሊያና በኤርትራ በመሄድ ነጻ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቢያመቻች መልካም እንደሆነም አንስተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ በሆስፒታሉና በተማሪዎቹ ምርቃት ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በቀጣይም ተማሪዎችና ሆስፒታሉ ስኬታማ የስራ ጊዜ እንዲኖራቸው ተመኝተዋል። የባህርዳር ዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር በለው ተገኝ ሆስፒታሉ ተመርቆ ስራ ቢጀምርም የህክምና መሳሪያዎች እንዳልተሟሉና ሆስፒታሉን ለማስተዳደር የሚያስችል የራሱ በጀት እንደሌለ ገልጸው መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ207 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ሲሆን ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ሲጀምር በቀን ሁለት ሺህ ህሙማንን የማስተናገድ አቅም አለው። ከዚህ በተጨማሪ ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ያህል ዜጎችን በቀጥታ ተጠቃሚ ማድረግ ይችላልም ተብሏል። ሆስፒታሉ 500 አልጋዎች የሚኖሩት ሲሆን 11 የቀዶ ህክምና ክፍሎች እንዳሉትና ቁጥራቸውን ወደ 15 የማሳደግ ዕቅድ እንዳለም ተገልጿል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም