በጋሞ ጎፋ ዞን ለውሾችና ድመቶች ክትባት መስጠት ተጀመረ

83
አርባምንጭ ግንቦት 15/2010 በጋሞ ጎፋ ዞን የእብድ ውሻ በሽታ ለመከላከል ለውሾችና ድመቶች ክትባት መሰጠት መጀመሩን የዞኑ እንስሳትና ዓሳ ሀብት መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያ ኃላፊው ዶክተር አፌወርቅ ከተማ ለኢዜአ እንደተናገሩት ክትባቱን ከአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር መሰጠት የተጀመረው የበሽታው ምልክት በዞኑ በተወሰኑ ከተሞችና ወረዳዎች በመታየቱ ነው። ምልክቱ ከታየባቸው ከተሞች መካከል አርባምንጭ አንዱ መሆኑን ገልጸው በሽታው ወደ ሰውና ሌሎች እንስሳት እንዳይተላለፍ ለመከላከል ከአንድ ሺህ በላይ ባለቤት ያላቸው ውሾችና 500 ድመቶች መከተባቸውን ገልጸዋል። ክትባቱን በሌሎች ወረዳዎች ለማስቀጠል ተጨማሪ የመድሃኒትና ኬሚካል ጥያቄ ለክልሉ መንግስት አቅርበው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። የዞኑ ጤና መምሪያ በበኩሉ በሽታው ከምልክት ባለፈ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እያደረስ ሲሆን በሽታውን ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃ በቂ አለመሆኑን ገልጿል። የመምሪያው ጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ባለሙያ  አቶ አንዳርጌ ቶቤ እንደገለፁት ከዞኑ ሶስት ወረዳዎች በበሸታው ተጠርጥረው ወደ አርባምንጭ ሆስፒታል የተላኩ አራት ታካሚዎች  በሽታው ተገኝቶባቸው ህይወታቸው አልፏል። ሞት በተመዘገበባቸው ወረዳዎች እስካሁን እርምጃ መወሰድ አለመጀመሩ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል። እርምጃው ክትባት ብቻ መሆን እንደሌለበትና ባለቤት የሌላቸው ውሾችና ድመቶችን ማስወገድን ጨምሮ በበሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራም መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል። በዞኑ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ የእንስሳት በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ባለሙያ ዶክተር ፀጋዓለም ኃይለሚካኤል በሰጡት አስተያየት 98 ከመቶ በሽታውን የሚያስተላልፉት ባለቤት የሌላቸው ውሾችና ድመቶች ናቸው፡፡ "ባለቤት የሌላቸው ውሾችና ድመቶች በሽታውን በምራቃቸው ለረጅም ጊዜ ይዞ ከሚያቆዩ ተኩላና ቀበሮ ከመሳሰሉ ዱር እንስሳት ጋር የመገናኘትና በበሽታው የመጠቃት እድላቸው ሰፊ በመሆኑ ነው" ብሏል። በእንስሳቱ የተነከሰ ወይም ከምራቃቸው የተነካካ ሰውም ሆነ የቀንድና ጋማ ከብቶችን ጨምሮ ፍየሎችና በጎች በበሽታው በቀላሉ እንደሚጠቃ ገልጸዋል። የአዕምሮ መታወክ በበሽታው ለተጠቁ ሰዎችና እንስሳቱ ዋነኛው ምልክት ሲሆን ውሾችና ድመቶች ውሃና ብርሃን መፍራት፣ መረበሽና መቆጣት ከአዕምሮ መታወክ አስቀድሞ የሚታዩ ምልክቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። በሽታው ወደ አዕምሮ መታወክ ከተቀየረ ህክምና አለመኖሩን ገልጸው በተጠረጠረ ውሻ የተነከሰ ሰው ከ24 ሰዓት ጀምሮ በመታከም ፈውስ ማግኘት እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡ በአርባምንጭ ዩኒቨርስት የእንስሳት ሃኪምና መምህር ዶክተር እድገት አባይነህ በበኩላቸው በሽታውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠርና መከላከል እንዳይቻል በሀገራችን የህግ ክፍተት መኖሩን ገልጸዋል። እብድ ውሻ በሽታ አደገኛና ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች አንዱ ቢሆንም የውሻ ባለቤቶች ውሾቻቸውን እንዲያሳውቁና በሽታ ሲከሰትም እንዲያስከትቡ የሚያስገድድ ህግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ይህ ህግ ያላቸው ሀገሮች በሽታውን በቀላሉ የመቆጣጠር እድል እንዳላቸው ገልጸው "በእኛ ሀገርም የሚመለከታቸው ህግ አውጪና አስፈጻሚ አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰብ አለባቸው" ብለዋል፡፡ በአርባምንጭ ከተማ ትላንትና ዛሬ ውሾቻቸውንና ድመቶቻቸውን ያሳከሙ ነዋሪዎች ሰርተፍኬት ወስደዋል፡፡ ባለቤት በሌላቸው ውሾች ላይ የሚወስደው እርምጃም እንደሚፋጠን ከዞኑ እንስሳትና አሳ ሀብት መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም