ካለሙት የቅመማ ቅመም የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አርሶ አደሮች ተናገሩ

106
አምቦ ህዳር 1/2011 የተደረገላቸውን ሙያዊ ድጋፍ ተጠቅመው ካለሙት ቅመማ ቅመም የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ በምዕራብ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ። በመኸሩ የእርሻ ወቅት በዞኑ በቅመማ ቅመም ከለማው መሬት 133 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርት ይጠበቃል። አርሶ አደር ቶልቻ በቀለ  በኤጀርሰለፎ ወረዳ የጨለለቃ ቦቤ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ  2010/11 የምርት ወቅት በአንድ ሄክታር ይዞታቸው ያለሙት አብሽ በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል። በግብርና ባለሙያዎች ታግዘው ለልማቱ ተገቢው ክትትልና እንክብካቤ እያደረጉ እንደሚገኙና  ከ16 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። የባኮ ወረዳ አርሶ አደር ቢተው መንገሻ በበኩላቸው በየዓመቱ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ከሚያለሙት በርበሬ ምርት ከ80 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኙ መሆኑን አስታውሰዋል። ባለፈው የእርሻ ይህንን አጠናክረው በመቀጠል ያለሙት  የበርበሬ ዛላው አያያዝ በጥሩ መሆኑ  20 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ አቅደዋል። “ነጭና ጥቁር አዝሙድ በዓመት ሁለት ጊዜ  እያመረትኩ ተጠቃሚ ሆኛለሁ “ያሉን ደግሞ የደንዲ ወረዳ አርሶ አደር አበበ መገርሳ  ናቸው። የቅመማ ቅመም ምርት በገበያ ላይ ከሌላ ሰብል ይበልጥ ተፈላጊነቱ እያደገ በመምጣቱ በዚህ ተበረታተው ማልማታቸውን እንደቀጠሉ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በአራት ጥማድ መሬታቸው ላይ ያለሙትን የቅመማ ቅመም ሰብል ከአረምና ከተባይ ለመከላከል እየተንከባከቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። በዞኑ ቡናና ሻይ ግብይት ባለስልጣን ጽህፈት ቤት የቡናና ሻይ ግብይት ባለሙያ አቶ አምበርብር ታደሰ በ2010/2011 የምርት ዘመን 10 ሺህ 532 ሄክታር መሬት በቅመማ ቅመም መሸፈኑን አስረድተዋል። በልማት ጣቢያ ሰራተኞች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ከለማው ቅመማ ቅመም  መካከል በርበሬ፣ አብሽ፣ ጥቁርና ነጭ አዝሙድ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ በልማቱም ከ19 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ባለሙያው ጠቅሰው ካለሙት መሬትም 133 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ  ገልጸዋል። በምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፈው ዓመት በቅመማ ቅመም ከለማው ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ 100 ሺህ ኩንታል  ምርት መሰብሰቡ ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም