ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተመረቀ

154
ባህርዳር ህዳር 1/2011 የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዛሬ ተመረቀ። ሆስፒታሉን መርቀው የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ናቸው። ሆስፒታሉ ከ207 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ሲሆን ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ሲጀምር በቀን ሁለት ሺህ ህሙማንን የማስተናገድ አቅም አለው። ከዚህ በተጨማሪ ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ያህል ዜጎችን በቀጥታ ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል ተብሏል። ሆስፒታሉ 500 አልጋዎች የሚኖሩት ሲሆን 11 የቀዶ ህክምና ክፍሎች እንዳሉትና ቁጥራቸውን ወደ 15 የማሳደግ ዕቅድ እንዳለው ተገልጿል። ሆስፒታሉ ለባህርዳር እና አካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል ሶስተኛው ሆስፒታል ይሆናል ነው የተባለው። በመሆኑም በፈለገ ህይወት ሆስፒታል ላይ ያለውን ጫና በማቀለል የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ሆስፒታሉን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም