በምዕራብ ሸዋ ከ53 ሺህ ለሚበልጡ ልጃገረዶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው

85
አምቦ ጥቅምት 30/2011 በምዕራብ ሸዋ በሁለት ዙር ከ53 ሺህ ለሚበልጡ ልጃገረዶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት በዘመቻ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የክትባት ፕሮግራም አማካሪ አቶ አበራ ፊጣ ለኢዜአ እንደገለጹት የማህፀን ጫፍ ካንሰር ህክምና በአምቦ ሆስፒታል ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን በዞኑ በሚገኙ ስድስት ሆስፒታሎች ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተካሄደ ነው። በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ከህዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት በነጻ ለመስጠት ነው የታቀደው። በአገልግሎቱም ዕድሜያቸው 14 ዓመት የሆናቸው ከ53 ሺህ የሚበልጡ ልጃገረዶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ በሁለት ዙር በሚሰጠው ክትባት 2 ሺህ 426 የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች  ይሳተፋሉ። የክትባት ዘመቻው የሚካሄደው በዞኑ በሚገኙ 958 ትምህርት ቤቶች፣ የእምነት ተቋማት እና 91 ጤና ጣቢያዎች መሆኑን ፕሮግራም አማካሪ አስታውቀዋል፡፡ ከክትባቱ በተጓዳኝ ስለ በሽታው አስከፊነትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለህበረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራም ይካሄዳል። የአምቦ ከተማ ነዋሪ ታዳጊ ወጣት ከበቡሽ ንጉሴ በሰጠችው አስተያየት በሽታው ሳይታወቅ ለረጅም ዓመታት ሊቆይ እንደሚችል ከጤና ባለሙያ መረዳቷን ተናግራለች፡፡ መከላከያ ክትባት መሰጠቱ ጤናን ለመጠበቅ ወሳኝ በመሆኑ በአገልግሎቱ መጠቀም እንደምትፈልግ ገልጻለች። ሁለት ልጆቻቸውን የማህጸን ጫፍ ካንሰር ለማስከተብ መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ዝናሽ አበራ ናቸው፡፡ በሽታው ከመከሰቱ በፊት ክትባቱን መውሰድ ሴቶች ለበሽታው ያላቸውን ተጋላጭት እንደሚያስቀር ግንዛቤ እንዳላቸውና ሁሉም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም