በሰሜን ሸዋ አርሶ አደሮችን በሴፍቲኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

65
ፍቼ  ጥቅምት 30/2011 በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ዝናብ አጠር በሆኑ ቀበሌዎች ከ37 ሚሊዮን ብር  በሚበልጥ ወጪ አርሶ አደሮችን በሴፍቲኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው  በአምስት ወረዳዎች በሚገኙ  61 ቀበሌዎች  16 ሺህ 726 አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸውን በሴፍትኔት መርሃ ግብር በማሳተፍ  የልማት ስራ ማከናውን ተጀምሯል፡፡ ተሳታፊዎቹ  በልማት ቡድን በመደራጀት ከተሰማሩባቸው መስኮች መካከል አፈርና ውሃ ጥበቃ ፣አነስተኛ መሰኖ፣ ደን ልማትና የገጠር መንገድ ስራ ይገኙበታል፡፡ በጽህፈት ቤቱ የሴፍቲኔትና ቤተሰብ ጥሪት ግንባታ ኃላፊ አቶ ተሾመ አስፋው ለኢዜአ እንዳሉት ተሳታፊዎቹ  በተሰማሩባቸው መስኮች ባከናወኑት ስራ ልክ የገንዘብ ክፍያ  ያገኛሉ። በእንሰሳት እርባታና ማድለብ ፣በንብ ማነብ ፣በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ፣በአነስተኛ መስኖ ልማት ስራ እንዲሰማሩ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ለተበዳሪዎች ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በነፍስ ወከፍ ከ5 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻች ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው ዓመት ለሴፍትኔት መርሃ ግብር በተመደበ 29 ሚሊየን ብር ወጪ   የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ ከ13 ሺህ በላይ አባወራና ቤተሰቦቻቸውን በሀብት ፈጠራ ልማት በማሳተፍ ራሳቸውን እንዲችሉ እገዛ መደረጉን ጠቅሰዋል። ከ78 ኪሎሜትር በላይ የገጠር  ጠጠር መንገድ እና 1ሺህ 57 ሄክታር የአፈርና ድንጋይ እርከን በተሳታፊዎቹ ከተከናወኑት መካከል ይገኙበታል፡፡ በመርሃ ግብሩ ከተሳተፉት መካከል  ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸውን ከ10 ሺህ ብር በላይ በማድረስ የምግብ ዋስትናቸውን ያረጋግጣሉ ተብለው የተለዩ 6 ሺህ 410 አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው ከአንድ ወር በኋላ ለምረቃ እንደሚበቁ አቶ ተሾመ አስታውቀዋል። መርሃ ግብሩ  የአርሶ አደሩን  ስራና ገቢ የማግኘት ባህሉን በማጎልበት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው ተብሏል፡፡ በዞኑ ኩዩ ወረዳ የቄሲ ቀበሌ ነዋሪ  አቶ ጥላሁን ቦያ  በሴፍትኔት መርሃ ግብር  ለሁለት ዓመት  እንደተሳተፉ  በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡ ለረጀም ዓመታት የምግብ እህል እየቀረበላቸው ኑሮቸውን ሲገፉ መቆየታቸውን አስታውሰው በመረሀ ግብሩ በመሳተፍ ሰርተው ባገኙት ገንዘብ ራሳቸውን ችለው  ለመቋቋም እንደተዘጋጁ ጠቁመዋል ። አቶ ጥላሁን እንዳሉት በተመቻቸላቸው የብድር ገንዘብ እንስሳት በማርባትና በማድለብ በሚያገኙት የተሻለ ገቢ ኑሮቸውን ለመቀየር ተሰናድተዋል። ሌላው የዚሁ ቀበሌ የመርሃ ግብሩ  ተሳታፊ አርሶ አደር  ብርሃኑ ኦላና  ገንዘብ ለማግኘት  በሚያስችል የመንገድ ልማት ሥራ በመሳተፍ ራሳቸውን ለመቻል  ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሚያገኙትም ዕለታዊ ገቢ መቆጠብ ጀምረዋል። በቀጣይ በቁጠባ በሚያስቀምጡት ገንዘብ ከሚያገኙት ብድር ጋር በማቀናጀት በእንስሳት እርባታ በመሰማራት ኑሮቸውን ለማሻሻል እንደሚጥሩ አስረድተዋል። የሶስት ልጆች አባት እንደሆኑ የተናገሩት የግራር ጃርሶ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሰብስቢ አለሙ በበኩላቸው  በመሬት መንሸራተት ሳቢያ የእርሻ መሬታቸው በመጎዳቱ በመረሃ ግብሩ መታቀፋቸውን ገልጸዋል፡፡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ገቢን ለማግኘት ምርሃ ግብሩ ምቹ  ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ሀበት ለማፍራት እየጣሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኩዩ ፣ግራር ጃርሶ፣ወረ ጃርሶ ፣ጅዳና ወጫሌ ወረዳዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር  የምግብ ዋስትና ችግር እንዳለባቸው የተለዩ  የዞኑ አርሶ አደሮች በተያዘው ዓመት በመርሃ ግብሩ መካተታቸውን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም