በግብርናው ዘርፍ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት መረባረብ እንደሚገባ ተመለከተ

71
አዳማ ጥቅምት 30/2011 በሁለተኛው  የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትግበራ ቀሪ ጊዜያት በግብርናው ዘርፍ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት መረባረብ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ያዘጋጀው የፌዴራልና  ክልሎች የግብርና ልማት አመራር አካላት ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በዚህ ወቅት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን እንደገለጹት የግብርና ዘርፍ ለኢኮኖሚው ዕድገት አበረታች ውጤቶች ቢያስገኝም በትራንስፎርሜሽን ዘመኑ በታቀደው መጠን ያሳካ አይደለም። በዋና ዋና የሰብል ምርታማነትን በሄክታር 25 ኩንታል በማድረስ ዓመታዊ ምርት  290 ሚሊዮን ኩንታል  መድረሱን አመልክተው ይህም ከዘርፉ ግብ አንፃር የ29 ሚሊዮን ኩንታል ጉድለት ማሳየቱን አስታውቀዋል ለዚህም ዋናው ችግር በፌዴራል፣በክልሎችና በሴክተሩ ውሰጥ የሚታዩ ያለመናበብ፣የምርት ማሳደጊያ ግበዓቶችን አቅርቦት ክፍተትና ወቅቱን ጠብቆ አሰራሮችን ያለማሻሻልን ጠቅሰዋል። በአገር ውስጥ የሚመረቱና ከውጭ ለሚገቡ የእርሻ መሳሪያዎችና ሌሎችም ግብዓቶች የማበረታቻ ስርዓቱ ያለመሟላትና  የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በተወሰኑ መስኮች ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ ሌላው ለውጤቱ ማነስ የተመለከተ ክፍተት ነው፡፡ በቀሪ ጊዜያት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ከሁሉም በፊት አስፈፃሚ አካላት የተናበበ፣በእውቀት ላይ የተመሰረተና ውጤትን ማዕከል ያደረገ አመራር መስጠት እንደሚገባ ሚኒስትሩ አመልክተዋል። በበጋ መስኖ ፣ በበልግና በመኽር የኩታ ገጠም የእርሻ ሥራ ላይ  በስፋት መረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል። በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ድልነሳው በበኩላቸው በ2011 መጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት የኤክስቴንሽን አገልግሎትን ለማጠናከር ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በግብርናው መስክ የተሰማሩ ከ3   ሚሊዮን በላይ እማወራና አባወራ አርሶ አደሮች በልማት ቡድኖች  በማደራጀት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማስገባት ተችሏል፡፡ በክልሉ በ2010/11 ምርት ዘመን በተለያዩ ሰብል ከለማው 4ሚሊዮን 400 ሺህ  ሄክታር  መሬት ላይ ከ110 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ መጤ አረም በክልሉ እየተስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት ክልሉ በዘር ራሱን ለመቻል እያደረገ ያለውን ጥረት በመፈታት ችግር እንደሆነባቸውም ጠቅሰዋል፡፡ በደቡብ ክልል በ2010/11 የምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው 874 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 55 በመቶው  በተሟላ ፓኬጅ የተዘራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸው፡፡ ከለማው መሬትም 46 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚበቅ አመልክተው እስካሁን በክልሉ በግብርና ኤክስቴንሽን 2ሚሊዮን 300ሺህ  አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ የፌዴራልና የክልሎች የ2010/11 የምርት ዘመን እቅድ አፈጻጸም ላይ በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም