የእምነት ተቋማትና ተከታዮቻቸው የጥላቻ አስተምህሮዎችን ለመከላከል በጋራ ሊሰሩ ይገባል

92
አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2011 በሃይማኖት ስም የሚነዙ የጥላቻ አስተምህሮዎችን ለመከላከል የእምነት ተቋማትና ተከታዮቻቸው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ። መንግስት ከሃይማኖት ተቋማት አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ሊቆጣጠር እንደሚገባም ተነገሯል። ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች በመከባበር በጋራ የኖሩባት ብትሆንም አሁን አሁን በሃይማኖት ስም የሚሰራጩ የጥላቻ አስተምህሮዎችና ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው። ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ችግሩን በየዕምነት ተቋማቱ መፍታት ካልተቻለ ወደከፋ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። ሃይማኖቶች ከሰው ፍጥረት ሁሉ ጋር በፍቅር መኖርን መሰረት አድርገው የሚመሩ ቢሆንም አንዳንድ የግል ፍላጎትና ጥቅም ያላቸው ግለሰቦች ሃይማኖትን ማዕከል በማድረግ ግጭት የሚያስነሱ የጥላቻ መልክዕቶችን እየነዙ ነው። ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የጥላቻ አስተምህሮው እንደየሰዉ አመለካከት የሚለያይ መሆኑን ገልጸው ከራስ ውጪ ላለ እምነት ጥላቻ መያዝና ያንንም በንግግር የመተገበር ሁኔታ እንደሚታይ ጠቁመዋል። ይህ የማዕከላዊነት አስተሳሰብ እጥረት የሚፈጥረውና ከግል ፍላጎት የሚመነጭ እንጂ በሃይማኖት አስተምህሮ የሌለ መሆኑንም ገልፀዋል። 'ችግሩ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዓለማትም የሚስተዋል ሲሆን በአብዛኛው የአሸባሪነት መነሻውም ይህ ነው' ብለዋል። ቄስ ዶክተር ኪሮስ ላቀው በበኩላቸው ችግሩ አጠቃላይ ባይሆንም የራሳቸውን ሃይማኖት አብልጠው ሌላውን የሚያንቋሽሹና የግል ሃሳብ ያላቸው አስተማሪዎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት። ችግሩን ለማስወገድ እንደ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢኖርም ተቋማት ላይ አስከብሮ መሄድ ጋር 'ክፍተት' አለ ብለዋል። ጉዳዩ በሃይማኖት የተከለከለ ብቻ ሳይሆን በህግም ጭምር የሚያስጠይቅ መሆኑን በመጥቀስ። በማህበራዊ ሚዲያ በክርስትናና እስልምና ስም የጥላቻ ዘር እየዘራ በሃይማኖቶች መካከል መቃቃር እንዲኖር የሚሰራ ሌላ ፍላጎት ያለው አካል መኖሩን የተናገሩት ደግሞ ሼህ ኡመር ኢማም ናቸው። የሃሰትና የጥላቻ ሰባኪዎች አስተምህሯቸው እየሰፋ ለሰው ልጆች ህይወትና ለሰላም መጥፋት ምክንያት እየሆነ መጥቷልም ነው ያሉት። ይህን ችግር ለማስወገድ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የጀመራቸው ስራዎች መኖራቸውን የገለጹት መጋቢ ዘሪሁን ደጉ ባለፈው ዓመት ከተለያዩ ኃይማኖቶች የተውጣጡ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያሳተፈ ስልጠና መሰጠቱን አንስተዋል። እንደ ተቋም የሰላምና የአንድነት ማስተማሪያ የጋራ ማኑዋል ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ቢገባም አተገባበር ላይ በየሃይማኖት ተቋማቱ ልዩነት እንደሚንፀባረቅ ተናግረዋል። በሃይማኖት ተቋማት ስር ያሉ መምህራንን የማስተማርና የመገሰፅ ብሎም የመቅጣት ኃላፊነት በሃይማኖት አባቶች ላይ የሚጣል አደራ መሆኑንም ገልፀዋል። መንግስትም በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ 'የዚህ እምነት ተከታይ ነኝ' በሚል የሚለቀቁና ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮችን የሚቆጣጠርበት አሰራር ቢዘረጋ ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል። አማኞችም ከእምነት ተቋማት ውጪ የሆኑ የጥላቻ አስተምህሮ የሚነዙ ግለሰቦች ሲያጋጥሟቸው ማስተዋልና ድርጊቱን ማውገዝ እንደሚኖርባቸው መክረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም