የከተሞችን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ለማሻሻል የንቅናቄ መድረክ ተጀመረ

411
ደብረብርሃን  ጥቅምት  30/2011 የከተሞችን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ግልፅና ተደራሽ ለማድረግ የንቅናቄ መፍጠሪያ መድረክ ተጀመረ። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከፌዴራልና ክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ማሻሻያ ህዝባዊ የንቅናቄ መፍጠሪያ መድረክ በደብረብርሃን ከተማ ተጀምሯል። ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በ142 ከተሞች ደረጃውን የጠበቀ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ማለትም በመሬት ልማትና አስተዳደር፣ በግንባታ ፍቃድ አሰጣጥ፣ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣ አሰባሰብና አወጋገድ፣ በመፀዳጃ ቤትና ቄራ አገልግሎት፣ በእሳት አደጋ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም ዘላቂ ማረፊያ ላይ ሲሰራ ቆይቷል። ይሁንና የትግበራ ሂደቱ በአገልግሎት ስታንዳርዶች አይን ሲታይ አዝጋሚና በአብዛኛው ከተሞች ተደራሽ እንዳልነበር ገልፀዋል። አገልግሎቱን ለመስጠትም የአገልግሎት ሰጪዎች ግዴታን እንዲሁም የህዝቡን የአገልግሎት ተጠቃሚነት ግልፅ፣ ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተደራሽ እንዲሆን ህዝባዊ የንቅናቄ መድረኮች ይካሄዳሉ ብለዋል። በሌላ በኩል በከተሞች ያለውንጀ ሰነድ አልባና ህገወጥ ይዞታዎችን ስርዓት ለማስያዝ የዝግጅት ምዕራፍ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቂያ የህዝባዊ መፍጠሪያ ሰነድ መዘጋጀቱንም አንስተዋል። በከተሞች የሚሰጡ አገልግሎቶች የተለያዩ ቢሆኑም ኀብረተሰቡን ያማረሩ ሆነው ቀጥለዋል ያሉት ሚኒስትሩ ኀብረተሰቡ ከራሱ የሚጠበቅበትን ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል። የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ስርዓትን ከፌዴራል እስከ ከተሞች ለመምራት የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደስራ ቢገባም ኀብረተሰቡ በባለቤትነት ካልመራው ውጤታማ እንደማይሆን ነው የተናገሩት ። ህገወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን በመከላከል ለነዋሪዎች ምቹና ፅዱ ከተሞችን ለመፍጠር በባለቤትነት የሚመራ ተቆርቋሪ ማህበረሰብ መፍጠረ ይገባልም ነው ያሉት። በከተሞች የሚደረጉ የንቅናቄ መድረኮችም በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትም ሆነ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት በኩል ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት ከኀብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ለመፍጠር ያግዛልም ብለዋል። በኢትዮጵያ ካሉ 2 ሺህ 25 ከተሞች ውስጥ ስታንዳርዱን የጠበቀ አገልግሎት ይዘው ወደተግባር እንዲገቡ የተደረጉት 142 ብቻ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም