የህዝብ ተጠቃሚነትንና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ለውጡን ለማስቀጠል እንሰራለን.... የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች

73
ደሴ  ጥቅምት 30/2011  የህዝብ ተጠቃሚነትንና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች ገለጹ፡፡ የዞኑ የ2011 በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ንቅናቄ ዕቅድ ለማስተዋወቅ የተዘጋጀው መድረክ በደሴ ከተማ ወሎ ባህል አምባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የዞኑ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፀሐይ ረጋሳ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ሀገራዊ ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና የህግ የበላይነትን የሚስከብሩ ሥራዎችን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በስፋት መፈጸማቸው፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መስተዋላቸውና ለልማት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ አለመስጠት በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል። በመሆኑም ይሄን አሰራር በመቅረፍ ህዝቡን ለመካስ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ነው ያረጋገጡት። " በአሁኑ ወቅት የተገኘውን አገራዊ ለውጥ ማስቀጠል የሚቻለው ነባሩ አመራር የሰራቸውን ስህተቶች ባለመድገምና ተጠያቂነት ያለው አሰራር መተግበር ሲቻል ነው " ያሉት ደግሞ የዞኑ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊ መኮንን ናቸው፡፡ ነባሩን አመራር በጅምላ በአጥፊነት መፈረጅ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸው ከለውጡ ጋር የሚራመድ ብቁ መሪ ለመፍጠር በሳይንስ የተደገፈ የአመራር ክህሎት ስልጠና መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ህዝቡም ለለውጡ አስተዋጽኦ ያደረገውን ያህል ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች በሙሉ በአንዴ ሊፈቱ እንደማይችሉ ተገንዝቦ አመራሩን ማገዝ እንዳለበት ገልጸዋል። የህዝቡን ጥያቄዎች መስማት ብቻ ሳይሆን ፈጥኖ ለመፍታትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የአዴፓ ሥራ አመራር ከክልሉ ውጭ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ፣ መፈናቀል፣ የሀብት ውድመትና የአካል ጉዳት እንዲቆም አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ የጠየቁት ደግሞ የዞኑ አሳ ሀብት ልማት ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አሻግሬ ናቸው ፡፡ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ በበኩላቸው ዞኑ አብዛኛው አመራሩን በአዲስ ኃይል መተካቱን ተከትሎ የክህሎት፣ የአመለካከትና የእውቀት ክፍተት ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ይሄን ችግር ለመፍታት ተቋማዊ ቁመና በማስያዝ በጥናት የተደገፈ ስልጠና ለአመራሩ እንደሚሰጥም አመልክተዋል፡፡ ከክልሉ ውጭ ባሉ የአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰውን መፈናቀልና ሌሎች ችግሮች ለመፍታት ፓርቲው ከፌደራልና የአማራ ተወላጆች ከሚኖሩባቸው ክልሎች መንግስታት ጋር ሆኖ እየሰራ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአማራ ክልል የሚኖሩ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች በክልሉ ስጋት ሳይገባቸው በሰላም እንዲኖሩ በማድረግ ለሌሎች አካባቢዎች አርአያ ለመሆን እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡ ዛሬ በተጠናቀቀው የውይይት መድረክ ላይ ከደቡብ ወሎ የተለያዩ ወረዳዎች የመጡ ከ600 በላይ አመራሮች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም