ህብረታቸውን አጠናክረው ለውጡን ለማስቀጠል እንደሚተጉ ሴቶችና ወጣቶች ገለፁ

64
ድሬደዋ ጥቅምት 30/2011 ህብረታቸውን አጠናክረው ከጥላቻ  በመራቅ በሀገሪቱ የተጀመረውን የፍቅርና የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል  እንደሚተጉ በምስራቅ ኢትዮጵያ  አስተያየታቸውን የሰጡ  ወጣቶችና ሴቶች ገለፁ፡፡ ከአምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች ጋር በመተባበር በድሬደዋ በተዘጋጀው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የሰላም ጉባኤ የተሳተፉት እነዚህ ወጣቶችና ሴቶች ለኢዜአ እንዳሉት ለአንድነት መጎልበት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው፡፡ ከሶማሌ ክልል ጅግጅጋ የመጡት ወይዘሮ አስሊ ከድር የምስራቁ ተጎራባች ህዝቦች ለሀገር ምሳሌ የሚሆን የፍቅር፣ የህብረት ፣ የይቅርታ እሴቶች ባለቤት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ እሴቶች በትውልድ ውስጥ እንዲሰርፁ በማድረግ ሀገራዊ ለውጡን ለማሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዋ እንዳመለከቱት ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት አሁንም በጅግጅጋ ገንዘብ እየበተኑ ሰላምን ለማደፍረስና ህዝብ እንዲጎዳ እየሰሩ በመሆኑ መንግስት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ፡፡ ይህን መሰል ጉባኤ በድሬዳዋ በመዘጋጀቱ በሰላም ጉዳይ፣ ወቅታዊና አንገብጋቢ ችግሮችን ለመረዳት መቻላቸውን የተናገሩት ደግሞ ከድሬደዋ አስተዳደር በጉባኤው የተሳተፉት ወይዘሮ ኑሪያ ሐሚዶ ናቸው፡፡ በከተማዋና ገጠር ከሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ለዘመናት የኖረውን  አንድነት ጸንቶ በዘላቂነት እንዲቀጥል እያስተማሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከኦሮሚያ የመጡት ወይዘሮ  ኪሚያ ኡስማኤል "የተፈጠረውን የርስ በርስ ጥላቻና የንቀት ንግግሮች በመተው በእርቅና በሰላም ለሁላችንም የምትሆን ሀገር የመገንባት ኃላፊነት አለብን " ብለዋል፡፡ እናቶች የቤተሰብንና የማህበረሰብ መሶሶ መሆናቸውን የተናገሩት መምህርት ሂንዲያ መሐመድ "የተሻለች ሀገር ለመገንባትና አንድነት እንዲጠናከር ሴቶች የማይተካ ሚናችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የሰላም ጉባኤ ይህን ኃላፊነት ይበልጥ ለመወጣት ያነሳሳቸው በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ባልደረቦቻቸው የጀመሩትን ሀገራዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡ ወይዘሮ ፋኪያ አብደላ በበኩላቸው " ሁሉም ብሔረሰቦች ህብረታቸውን አጠናክረው ሊበታትኑን የሚፈልጉ ጠላቶቻችን በጋራ በመከላከል የቀድሞ አንድነታችንን መመለስ ይገባናል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከአፋር ክልል የመጣው ወጣት አቢተው አይቲሌ አህመድ ወጣቶች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንደመሆናቸው የሚገጥሟቸውን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በመጠየቅ እንዲፈታላቸው መጣር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ " የአፋር ወጣቶች በሀገሪቱ የተጀመረው የአንድነትና የለውጡ ጉዞን ለማሳካት ከምንጊዜውም በላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ " ብሏል፡፡ ሌላው ከሐረሪ ክልል በጉባኤው የተሳተፈው ወጣት አብዱልሃሚድ አህመድ በበኩሉ ወጣቱ በሰላምና በሰከነ አእምሮ በመመራት ለሁሉም የምትበጅ ሀገር ለመገንባት የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት መትጋት እንዳለበት አመልክቷል፡፡ በተለይ ጥላቻን ከሚሰብኩና ህዝብ ከህዝብ ከሚያጋጩ ከማህበራዊ ሚዲያ አሉባልታዎች በመራቅ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር  የበኩሉን እንደሚወጣ  ተናግሯል፡፡ ‹‹በብዙሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት›› በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው ጉባኤው  የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ፣ ከምስራቅ ኦሮሚያ ፣ ከአፋር፣ ከሶማሌ፣ ከሐረሪ ክልሎችና ከድሬዳዋ አስተዳደር የተወጣጡ ወጣቶችና ሴቶች ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ዑጋዞችና  አባገዳዎች ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም