በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ከ3 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በኩታ ገጠም ሊለማ ነው

78
ሽሬ እንዳስላሴ   ጥቅምት 30/2011 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በመስኖ ልማት ከ3 ሺህ 500 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ሽንኩርትና ቲማቲም በኩታ ገጠም ለማልማት እየተሰራ ነው። በዞኑ አስተዳደር የመስኖ ልማት አስተባባሪ አቶ ሚኪኤለ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጋው ወቅት 7 ሺህ 520 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ወራጅ ወንዝና የጉድጓድ ውሃ በመጠቀም ከሚለማው መሬት ውስጥ 3 ሺህ 516 ሄክታሩ በቀይ ሽንኩርትና ቲማቲም በኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴ እንደሚለማ ገልጸዋል። "ይህም ባለፈው ዓመት በአንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው በኩታ ገጠም የማልማት ሥራ ዘንድሮ በሁለት እጥፍ ከፍ እንዲል ያደረጋል" ብለዋል አቶ ሚካኤል፡፡ በክላስተር ማልማት ምርቱ ጥራቱ የተጠበቁ እንዲሆን የሚያደርግ ከመሆኑ በተጨማሪ በጋራ የእርሻ ሥራውን ለመከታተልና ምርትን ወደ ገበያ ለማቅረብ ጠቀሜታ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡ ይህም የአርሶ አደሮችን የገበያ ችግር የሚፈታ መሆኑን ነው አስተባባሪው የገለጹት፡፡ እንደአቶ ሚካኤል ገለጻ በኩታ ገጠም ማልማት አርሶ አደሮች ከግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና የሙያ ምክር በቀላሉ አግኝተው ጥራትና ብዛት ያለው ምርት ለማምረት ያስችላቸዋል፡፡ " እርስ በርሳቸው እንዲደጋገፉና የምርት ማሳደጊያ ግብአት በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ በኩልም ጠቀሜታው የጎላ ነው" ብለዋል፡፡ በመጀመርያው ዙር በኩታ ገጠም በመስኖ ለሚያለሙ ከ7 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በልማቱ ላይ ስልጠና መሰጠቱንም አቶ ሚኪኤል ተናግረዋል፡፡ ስልጠናውን ከወሰዱት አርሶ አደሮች መካከል የመደባይ ዛና ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መብራህቶም ተስፋዬ እንዳሉት የመኽር ሰብላቸውን ፈጥነው በመሰብሰብ ወደ መስኖ ልማት ሥራ ለመግባት እየተዘጋጁ ነው፡፡ ሌላው የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ፍጹም አረጋይ በበኩላቸው "በስልጠናው በኩታ ገጠም ማልማት ያለውን ጠቀሜታ ተረድቺያለሁ" ብለዋል፡፡ በቀጣይም ፈጥነው ወደ መስኖ ልማት ለመግባት ሰብላቸውን በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ " በኩታ ገጠም ማልማት ሰብልን ከበሽታ ለመከላከልና የሙያ ድጋፍ ለማግኘት ጠቀሜታ ስላለው ማሳዬን በክላስተር ለማልማት እየሰራሁ ነው” ያሉት ደግሞ በታህታይ ቆራሮ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር እምብዛ መላኩ ናቸው። ባለፈው ዓመት ከ6 ሺህ 200 ሄክታር በላይ ማሳ በመስኖ በማልማት ከ350 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ታውቋል ሲል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም