በበጌዴኦ ዞንና አካባቢው የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እንሰራለን....የባህልና የሃይማኖት መሪዎች

98
ዲላ ጥቅምት29/2011 በጌዴኦ ዞንና አካባቢው የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የባህልና የሃይማኖት መሪዎች ገለጹ፡፡ የጌዴኦ ብሔር አባ ገዳ አማካሪ የሆኑት ጫዋጄ አለማየሁ ሂርቤ የብሔሩ ባህላዊ አስተዳደር የሆነው የገዳ ስርዓት መሰረቱ ሰላም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአስተዳደር ሥርዓት ከዚህ በፊት ተከስተው የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የበኩሉን ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖችና አጎራባች አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታትም ከዚህ በፊት ከነበሩ ልምዶች ተነስተው በርካታ ተግባራት ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ "ጌዴኦና ጉጂ ወንድማማቾች ህዝቦች ናቸው" ያሉት ጫዋጄ አለማየሁ በመካከላቸው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሁለቱም ህዝቦች ባህላዊ መሪ የሆኑት አባ ገዳዎች አንድ አቋም ይዘው በአንድ ላይ በመስራታቸው በጋራ በሚመሩባቸው የ"ጎንዶሮ" እና "ፋጬ" ሥርዓቶች መሰረት እርቀ ሰላም ለማውረድ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የተፈጠረው እርቅ ዘላቂነት እንዲኖረው የጌዴኦ አባ ገዳ መዋቅር ባሉት 525 ሸንጎዎች አማካይነት ህዝብን የማረጋጋትና የማቀራረብ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል ያሉት አማካሪው ከሃይማኖት መሪዎች ጋርም ጠንካራ ጥምረት በመፍጠር ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡ ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ከሚሰሩ አካላት ጎን በመቆም ባከናወኗቸው ተግባራት ውጤት በመታየቱ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂነት አንዲኖረው በቀጣይም የድርሻቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዲላ፣ ቡሌ፣ ወናጎና፣ ዳራ ወረዳዎች ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የጌዴኦ ዞን የሃይማኖት ጥምረት ሰብሳቢ መልዓከ ምህረት ቆሞስ አባ ታዬ ወርቁ እንደገለጹት ችግሩን ለመፍታት በዞኑ የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ጠንካራ ጥምረት በመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል፡፡ " የጸጥታ ችግሩን ከመፍታት ጎን ለጎን የተፈናቀሉ ወገኖችን የማጽናናትና ድጋፍ የማድረጉ ተግባርም ሁሉንም ያሳተፈ ነበር" ብለዋል፡፡ ህዝቡን ለማረጋጋትና እርቀ ሰላም ለማውረድ ከሁለቱም አባገዳዎችና ከመንግስት ጋር ተባብረው በመስራታቸው ውጤት መገኘቱንም አመልክተዋል፡፡ የተገኘውን ሰላም ቀጣይነት ለማረጋገጥም በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ መልዓከ ምህረት ቆሞስ አስረድተዋል፡፡ ከምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች የሃይማኖት ተቋማት ጋር የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው አክለው የገለጹት ፡፡ በዲላ ከተማ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌ የሆኑት አቶ ጢባ ማልደኒ የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ተቋማት መሆናቸውን ገልጸዋል። ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ባደረጉት ርብርብ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ በርካታ ዜጎች ተፈናቅለው በዞኑ ውስጥ መጠለላቸውን ተከትሎ በተፈጠረው ውጥረት ሰላም ይናጋል የሚል ሥጋት ውስጥ ገብተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጢባ ይህንኑ ለማርገብ በየቤተ እምነቱ የተሰሩ ሥራዎች ስኬታማ እንደነበሩ አስረድተዋል ፡፡ "በአካባቢው የተገኘው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው ከመንግስትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የምናደርገውን የጋራ ጥረት እናጠናክራለን " ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም