ለህጻናት የንባብ ክህሎት ማደግና ለኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት አሜሪካ የድርሻዋን ትወጣለች....የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር

73
ደብረ ብርሀን ጥቅምት 29/2011 ለህጻናት የንባብ ክህሎት ማደግና ለኢትዮጵያ ትምህርት ጥራት አሜሪካ የድርሻዋን እንደምትወጣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር ገለጹ። አምባሳደሩ ይህን የተናገሩት በኢትዮጵያ አምስት ዓመት የሚቆይ የንባብ ክህሎት ማሳደጊያ ፕሮጀክትን ዛሬ በሰሜን ሽዋ ዞን ባሶና ወራና ወረዳ በባቄሎ ትምህርት ቤት በይፋ ባስከፈቱበት ወቅት ነው፡፡ አምባሳደር ማይከል ሬነር እንደገለጹት የተማሪዎችን የንባብ ክህሎት በማሳደግ የትምህርት ጥራቱን ለማረጋገጥ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ትስራለች፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች 3 ሺህ ትምህርት ቤቶች ላይ 12 ሺህ የንባብ ጣቢያ ተዘጋጅተው ለንባብ ክፍት ይሆናሉ ብለዋል፡፡ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ፣ ሶማሌያና አዲስ አበባ ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው ክልሎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ለሥራ ማስፈጸሚያ፣ ለተለያዩ ቁሳቁሶችና መጻህፍት ማሟያም 86 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመደቡን ነው አምባሳደር ማይክል የገለጹት፡፡ ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመት የሚቆይ ሲሆን "ለ15 ሚሊዮን ህጻናት ተደራሽ" ይሆናልም ብለዋል፡፡ እንደ አምባሳደር ማይክል ገለጻ ለኢትዮጵያ የወደፊት እጣፈንታ ህጻናት ወሳኝ በመሆናቸው ከወዲሁ ጥሩ እውቀትና የአገር ፍቅር እንዲኖራቸው ወላጅና መምህራን ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሊረባረብ ይገባል፡፡ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው በሚከፈቱ የንባብ ጣቢያዎች የሚቀመጡ አጋዥ መጻህፍትን በማንበብ ህጻናት እውቀታቸውን አሳድገው ለትምህርት ጥራቱ መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ህብረተሰቡም ህጻናት ተማሪዎችን ትንሽ ደግፎ ትልቅ ነገር ለማግኘት ከመንከባከብ ጀምሮ በመደገፍና በመከታተል ጥሩ ደረጃ እንዲደርሱ የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል አምባሳደሩ ፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌጤ በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ እየቀነሰ ላለው የትምህርት ጥራት መጠበቅ  ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ከአሜሪካ ጋር ባደረገው ጥናት ህጻናት ተማሪዎች ከክፍል ክፍል መሸጋገራቸውን እንጂ በቂ እውቀት አለመያዛቸው ታውቋል። ከእዚህ ባለፈ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንኳ በትክክል ማንበብና መጻፍ የማይችሉ በርካቶች መሆናቸው በጥናቱ መረጋገጡን አመልክተዋል፡፡ "በመሆኑም ፕሮጀክቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በየክልሉ የሚዘጋጁት የንባብ ጣቢያዎች በቅርቡ ተጠናቀው ተማሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራል" ብለዋል፡፡ በየክልሉ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ተምረው የማንበብ፣ የመጻፍና የመናገር ክህሎታቸውን ከማሳደግ ባለፈ ሌሎች የአገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎችን በቀላሉ እንዲለምዱ በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ወላጆችም ተማሪዎች ትምህርት ቤት መመላለሳቸውን ብቻ ሳይሆን ምን እንደተማሩ፣ የት እንደዋሉና ምን እንዳወቁ በመከታተል ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ የሰሜን ሽዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አይነኩሉ አበበ በበኩላቸው "በዞኑ ባሶና ወራና፣ ቀወትና ሽዋ ሮቢት ሦስት ወረዳዎች ተመርጠው በ12 ትምህርት ቤቶች ላይ እያንዳንዳቸው አራት የንባብ ጣቢያ ይሰራላቸዋል" ብለዋል፡፡ በንባብ ጣቢያዎቹ በቂ ቁሳቁስ በማሟላት ተማሪዎች እሁድና ቅዳሜን ጨምሮ ትርፍ ጊዜያቸውን ተጠቅመው የንባብ ክህሎታቸው እንዲያሳድጉ አስነባቢዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ በፕሮጀክቱ መክፈቻ ላይ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብና የአዲስ አበባ ክልሎች ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም የክልልና የዞን ትምህርት ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም