በጋምቤላ ከተማና አካባቢዋ ያለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ስጋታችንን አስወግዶልናል….የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ነባር ተማሪዎች

896

ጋምቤላ ጥቅምት 29/2011 በጋምቤላ ከተማና አካባቢዋ ያለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ወደ ዩኒቨርሲቲው ከመምጣታቸው በፊት የነበረባቸውን የፀጥታ ስጋት እንዳስወገደላቸው የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ነባር ተማሪዎች ገለጹ፡፡

ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ለኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች  እንዳሉት ወደተቋሙ ከመምጣታቸው በፊት በጋምቤላ ከተማና አካባቢዋ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ስጋት ገብቷቸው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ወደዩኒቨርሲቲው ከመጡ በኋላ ያለው የከተማዋ ሁኔታ የሰጉትን ያህል እንዳልሆነና ከበፊቱ ያልተለየ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን እንዳስተዋሉ ተናግረዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ተማሪ ከድር ቀኒሳ እንዳለው ወደዩኒቨርሲቲው ከመምጣቱ በፊት በአካባቢው የፀጥታ ችግር ይኖራል የሚል ስጋት የነበረበት ሲሆን ወደአካባቢው ከመጣ በኋላ ሁሉም ነገር ሰላማዊ መሆኑን እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡

ተማሪው አክሎ ከዚህ ቀደም ወደዩኒቨርሲቲው ሲመጣ የትራንስፖርት ችግር አጋጥሞት እንደነበረና በዚህም ከታሪፍ በላይ ለመክፈልና ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጦ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ከመቱ ከተማ ጀምሮ የትራንስፖርት አገልግሎት በማዘጋጀቱ ችግሩ መፈታቱንና በእዚህም ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተደረገልን አቀባበል ከበፊቱ የተለየና በአካባቢው ያለው እንቅስቃሴም ሰላማዊ መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ተማሪ ሰላማዊት ብርሀኑ ናት፡፡

ሌላዋ ተማሪ ጫልቱ ተስፋዬ በበኩሏ በቅርቡ በጋምቤላ ክልል ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር አካባቢው ሰላም ላይሆን ይችላል በሚል ወደዩኒቨርሲቲው ለመምጣት ሰግታ እንደነበር ተናግራለች።

በአሁኑ ወቅት ስጋቷ መወገዱን የገጻ  በዩኒቨርሲቲው በተደረገላት አቀባበል ደስተኛ መሆኗንና የዘንድሮ አቀባበል ከበፊቱ የተሻለ ዝግጅት የተደረገበት ስለመሆኑ መታዘቧን ተናግራለች።

ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አቀባበል ሲያደረጉ የነበሩት የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ተማሪዎችን ከመቀበል ባለፈ በቀጣይም የመማር ማስተማሩን ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ከተማሪዎች ጎን በመሆን የበኩላቸውን እገዛ አንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ከነዋሪዎች መካከል አቶ ኬት ማቲዎስ በሰጡት አስተያየት ለዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማሩን ሂደት ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡ ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እንዲመለሱ ሁላችንም ጥረት እናደርጋለን ያሉት ደግሞ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ፓስተር ፒተር አጉዋ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከጥቅምት 26 ቀን ጀምሮ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ነባር ተማሪዎችን የተቀበለ ሲሆን ዛሬና ነገም ከ1 ሺህ 500 መቶ በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ታውቋል፡፡