በአሮሚያ የግብርና ዘርፉን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

927

አዳማ  ጥቅምት 29/2011 በኦሮሚያ ክልል የግብርና ዘርፉ ኢንዱስትሪውን መመገብ በሚችልበት መልኩ ለማዘመን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የክልሉን ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማትና እድገት በህዝባዊ ተሳትፎ ለማጠናከር የተዘጋጀው  የንቅናቄ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የግብርና ሴክተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የግብርና ዘርፉ ኢንዱስትሪውን በበቂ ሁኔታ መመገብ እንዲችል ተቋማዊ አደረጃጀትና አሰራርን ለማዘመን እየተሰራ ነው።

ይህም በዘርፉ አዳዲስ አሰራርና የቴክኖሎጂ ግኝቶችን ማላመድ፣ማባዛትና ለአርሶ አደሩ ማሰራጨትን የሚያካትት ነው፡፡

በተለይም በሰብል ልማት ላይ ብቻ በስፋት ሲሰራ የቆየውን  የተሻሻለ አሰራር በጥናትና ምርምር በአግባቡ በመደገፍ በቡና፣ በእንስሳት ፣በመስኖና ተፈጥሮ ሀብት ልማትና አያያዝ ጭምር ለማከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣የምርምር ማዕከላትና ተቋማት፣በሀገር ውስጥና በውጭ በዘርፉ ከሚሰሩ  የክልሉ  ምሁራን  ጋር በቅንጅት ለማሰራት የሚያስችል አመቺ  አሰራርና አደረጃጀት  መሆኑን አስረድተዋል።

“በዚህም የክልሉን ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማትና ዕድገት ከማፋጠን ባለፈ ዘርፉ ኢንዱስትሪውን በአግባቡ መመገብ በሚችልበት መልኩ ለማዘመንና ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለመ ግብ አስቀምጠን ርብርብ እያደረግን ነው “ብለዋል።

አርሶና አርብቶ አደሩን በቴክኖሎጂ መቅዳት፣ማላመድ፣ማባዛትና ማሰራጨት ዙሪያ  ሙሉ ተሳታፊ ይሆናሉ።

“አደረጃጀትና አሰራርን ብቻ በመዘርጋት በዘርፉ ለውጥ ማምጣት አይቻልም “ያሉት ዶክተር ግርማ ምሁራኑን፣ የባለሙያውንና የህብረተሰቡን አቅም አቀናጅቶ በማንቀሳቀስ ላይ ያለውን ከፍተት ለማስወገድ ትኩረት መሰጠቱን  አመልክተዋል።

የመድረኩ ዓላማ ከሁለተኛ ሩብ የበጀት ዓመት ጀምሮ በግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ፣በመስኖ ፣በቡናና ሻይ፣በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና  የእንስሳት ዘርፍ ልማት በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን እንደሆነ የገለጹት የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊው አቶ ዳባ ደበሌ ናቸው።

የተፈጥሮ ሀብቱ ልማት ሳይንሳዊ አሰራርን በተከተለ መልኩ እንዲከናወንና በሌሎችም የልማት ዘርፎች ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መድረኩ አሁን ላይ የደረሰውን ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ  ህዝቡ በደቦ እንዲያነሳና የማጨጃ ማሽነሪዎችን ተጠቅሞ በወቅቱ እንዲሰብሰብ ንቅናቄ ለመፍጠር ጭምር  መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ጽሁፍ  ያቀረቡት በቢሮው የኤክስቴንሽን ስርጻት ባለሙያ አቶ አያና ምርከና በበኩላቸው የግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎት ላይ የሚታየውን ክፍተት ለማስወገድ በስድስት  ዞኖችና 18 ወረዳዎች ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም የግብርና አሰራር ሥርዓት ከፍተት ያለበት መሆኑ፣በልማት ጣቢያ ሠራተኞች ዘንድ የአስተሳሰብና የአመለካከት ማነቆ መኖሩ አርሶ አደሩ የተሟላ የግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎት በአግባቡ እንዳያገኝ ችግር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የግብርና ሠርቶ ማሳያ ማዕከላት ለአርሶ አደሩ ተገቢውን የተግባርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም ግንባታ እንዲሰጡ በግብዓት ማጠናከርና በቂ ግልጋሎት እንዲሰጡ ማድረግ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ባለሙያው አሳስበዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ከክልሉ 20 ዞኖችና ከ300 ወረዳዎች የተወጣጡ ከ1ሺህ በላይ የዘርፉ ባለሙያዎች፣አመራሮችና ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ነው።

በግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ፣በመስኖ ልማት፣በቡናና ሻይ፣በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ እንዲሁም በእንስሳት ዘርፍ ልማት በቅንጅት ማከናወን በሚቻልበት ላይ መድረኩ የሚያተኩርባቸው ናቸው።